“የአገው ልክ ሰብዓዊነት እና ኢትዮጵያዊነት ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

14

ባሕር ዳር: ጥር 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 86ኛው የአገው ፈረሰኞች በዓል በእንጅባራ ከተማ እየተከበረ ነው። በዓሉ “የአብሮነት ቅርስ፣ የሰላም ውርስ” በሚል መሪ መልዕክት ነው እየተከበረ የሚገኘው።

በክብረ በዓሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚህ ታሪካዊ በዓል ላይ ስንቆም ሁለት ነገሮች በዐይነ ኅሊናችን ይመጣሉ፤ በአንድ በኩል ፈረስ ለኢትዮጵያ ታሪክ የዋለው ውለታ፤ በሌላ በኩል ይህን ውለታ ለማስታወስ የአገው አባቶች የሠሩት መታሰቢያ ነው ብለዋል።

የዛሬ 86 ዓመት ጣሊያን ከኢትዮጵያ በመውጣት ዋዜማ ላይ በደረሰበት ጊዜ የአገው አባቶች አንድ ነገር መከሩ፤ ፋሽስት ኢጣሊያ ሀገራችንን ሲወር አባቶቻችን የዘመቱት በፈረስ ጉልበት፤ በጦር አንደበት ነው፤ ይሄንን ውለታ ዘወትር ልንክረው ይገባል በሚል ነው ያሉት።

መክረው ዘክረው የፈረሰኞችን በዓል ከፈረሰኛው ጊዮርጊስ በዓል ጋር አስተሳስረው ሠሩት፤ ይሄው ዛሬ የፈረሰኞችን በዓል እያከበርን ነው፤ አባት ያበጀው ለልጅ ይበጀው ማለት ይህ ነው ብለዋል።

ይሄን በዓል እንድናከብር ላስጀመሩት እና ላስቀጠሉት የአገው አባቶች እና አለቆች ምስጋና ይገበቸዋል ነው ያሉት። ፈረስ በአገው ዘንድ አድራሽ፣ አራሽ፣ አዋጊ፣ የክብር መጎናጸፊያ ነው ብለዋል።

ለትራንስፖርት፣ ለእርሻ፣ ለጦርነት እና ለክብር ይገለገሉበታል፤ ይህም በመኾኑ ፈረስ ሰርግን፣ ክርስትናን፣ ለቅሶን፣ ክብረ በዓልን ያጅባል፣ ያደምቃል ነው ያሉት። የአገው ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ በዕለት ከዕለት ሕይዎቱ በሃዘኑ እና በደስታው ፈረስን ከተፈጥሮ ጋር እያዛመደ ይጠቀምበታል ብለዋል።

የአገው ፈረሰኞች በዓል የተጣሉት የሚታረቁበት የእርቅ ሥርዓት እንዳለውም ተናግረዋል። ፈረስ እና ኢትዮጵያ የሺህ ዘመናት ትስስር እንዳላቸውም ገልጸዋል።

ከጥንት ጀምሮ ፈረስ እና የኢትዮጵያ ነጻነት እየተሳሰሩ ይገኛሉ ብለዋል። የኢትዮጵያ የወል ትርክት ከሚኾኑት አንዱ ፈረስ እና ፈረሰኛነት ነው፤ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ፈረስ እና ፈረሰኛነት የኢትዮጵያውያን ሁሉ ባሕል እና ምልክት ነው ብለዋል።

በሲራራ ነጋዴዎች አማካኝነት የኢትዮጵያውያን ቋንቋዎች፣ ባሕሎች እና የወግ ዕቃዎች ያስተሳሰሩት ፈረሶቻችን እና በቅሎዎቻችን ናቸው ነው ያሉት። የዛሬዋን ኅብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያ መሥራታቸውንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን ፈረሰኞች ጠላትን ድል ሲያደርጉ መኖራቸውንም አንስተዋል። በኢትዮጵያ የነጻነት ተጋድሎ ውስጥ የፈረስ አና የፈረሰኞች ተጋድሎ ከፍተኛ እንደኾነም ገልጸዋል። የአገው ሕዝብ ኢትዮጵያን ከጠላት የተከላከሉ ፈረስ እና ፈረሰኞች የተገኙበት እንደኾነም ተናግረዋል።

የአገው ፈረሰኞች ወራሪ ጠላትን መሄጃ መቀመጫ ማሳጣታቸውንም ገልጸዋል። ዛሬ ላይ እኛ ልጆቻቸው የአገው አባቶቻችንን እናመሰግናቸዋለን ነው ያሉት። የፈረሶቻችን ታሪክ የወል ትርክታችን አካል ነው፤ የፈረሶቻችን ታሪክ የጋራ መስዋዕትነታችን ምስክር፣ የትስስራችን አርማ ነው ብለዋል።

የፈረስ ታሪክ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ታሪክ መኾኑንም
ተናግረዋል። ፈረሶቻችን አስተሳስረውናል፤ ሰሜኑን ከደቡብ፣ ምሥራቁን ከምዕራብ አያይዘውታል ነው ያሉት። ለጋራ ሀገራችን ለኢትዮጵያ በጋራ የከፈልነውን መስዋዕትነት ይነግሩናል ብለዋል።

በአገው ፈረሰኞች በዓል ከሊቅ እስከ ደቂቅ የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማ ከፍ አድርጎ እንደሚያውለበልብ ተናግረዋል። “የአገው ልክ ሰብዓዊነት እና ኢትዮጵያዊነት ነው”፤ አገው በእናት ሀገሩ እና በኢትዮጵያዊነቱ አይደራደርም፤ ኅብረ ብሔራዊ አርማ ያለውን ሠንደቅ ዓላማው ከፈረሱ በላይ ከፍ አድርጎ የሚያሳይ ጀግና እና ኩሩ ኢትዮጵያዊ ሕዝብ ነው ብለዋል። የሀገር ልኬታውም ይሄ መኾኑን ገልጸዋል።

ወደፊት በዚህ በዓል ከሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ፈረሰኞች እየመጡ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የሚጎለብቱበት በዓል እንዲኾን ምኞቴ ነው ብለዋል። ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን አልታያቸው ብሎ ከሚሰቃዩት ሴረኞች ይልቅ ፈረሶቻችን ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ከፍ አድርገው ያሳዩናል ነው ያሉት።

ፈረሶችን አልምደን፣ ገርተን እና አሠልጥነን ለነጻነት እና ለሉዓላዊነት እንደተጠቀምን ሁሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ፈጥረን፣ ገርተን እና ከሀገራችን ሁኔታ ጋር አዛምደን የምንጠቀምበት ዘመን ላይ እንገኛለን ብለዋል።

ፈረሶቻችን ምድሩን እንዳዳረሱት ሁሉ መኪኖቻችን ቀጣናውን፣ አውሮፕላኖቻችን ሰማዩን፣ መርከቦቻችንም ባሕሩን፣ ምርቶቻችን ገበያውን ማዳረስ ይገባቸዋል ነው ያሉት። የትኛውም የጨነገፈ አስተሳሰብ ከኢትዮጵያ ብልጽግና አያስቀረንም ብለዋል።

የአገው ሕዝብ እንደ አባቶቹ ጽንፈኝነትን እምቢ ያለ ሕዝብ መኾኑንም ተናግረዋል። የራሱን ባሕል እና ማንነት አክብሮ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር እንዴት መኖር እንደሚቻል መማር የፈለገ ሁሉ አዊ እንዲመጣ እጋብዛለሁ ነው ያሉት። የአገው ሕዝብ ሰላምን በራሱ እጅ እንዴት ማስጠበቅ እንደሚቻል በተግባር ማሳየቱንም ተናግረዋል።

የአገው ሕዝብ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ በፈረስ ጉልበት እንዲፈጥንም አስገንዝበዋል። ለኢትዮጵያ ብልጽግና እንደሚሠሩም ተናግረዋል። የአገው ፈረሰኞች በዓል የአገው ሕዝብ ቋንቋ፣ ባሕል፣ ታሪክ፣ ቅርስ፣ ወግ እና ሥርዓት በአደባባይ ለዓለም የሚያሳይ ግልጽ ሙዚየም ነው ብለዋል።

ሰላማቸውን እያስከበሩ አዊን የልማት መሶብ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል። የአገው ፈረሰኞች በዓል በዩኔስኮ እንዲመዘገብ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል፤ በጋራ እንደሚሳካም ገልጸዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“መቅደላ አፋፉ ላይ ጩኸት በረከተ የሴቱን አናውቅም ወንድ አንድ ሰው ሞተ”
Next article45 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ብድር ማሰራጨቱን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደብረ ብርሃን ዲስትሪክት አስታወቀ።