“መቅደላ አፋፉ ላይ ጩኸት በረከተ የሴቱን አናውቅም ወንድ አንድ ሰው ሞተ”

38

ደሴ: ጥር 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ አይበገሬነት እና የእጅ አልሰጥም ባይነት ታሪክ የተጻፈበት ታሪካዊ ቦታ ነው መቅደላ አምባ።

“የመቅደላ አምባ ታሪካዊ ቦታ ቅርስ እና አካባቢ ጥበቃ ለዘላቂ የቱሪዝም ልማት” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ የምክክር እና የፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በደሴ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ካሳ ሻወል (ዶ.ር) የደቡብ ወሎ ዞን በርካታ ታሪካዊ ስፍራዎች ያለበት እና በባሕላዊ እና በሃይማኖታዊ እሴቶቹ የሚታወቅ መኾኑን ተናግረዋል። ይህንን ታሪክ እና ቅርስ ለትውልድ ለማስተላለፍ ዩኒቨርሲቲው ኀላፊነቱን ለመወጣት የተነደፈ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

የመቅደላ አምባ ታሪካዊ ስፍራ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ድርሻ ያላቸው የአጼ ቴዎድሮስ የተጋድሎ ቦታ በመኾኑ አካባቢውን በማልማት የቱሪስት መዳረሻ ማድረግ ለነገ የማይባል ተግባር እንደኾነ ነው የገለጹት።

በመርሐ ግብሩ ላይ ከታደሙት መካከል የወሎ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር እና ተመራማሪ አሰፋ ባልቻ (ዶ.ር) መቅደላ አምባ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የአይበገሬነት እና እጅ ያለመስጠት፤ የአንድነት ተምሳሌት እና አልገዛም ባይነትን የሚያስታውስ ትልቅ የታሪክ አምባ መኾኑን አስረድተዋል።

ታሪኩን በማስታወስ አካባቢውን ለዘላቂ የቱሪዝም ልማት ተጠቃሚነት መሥራት ከኢትዮጵያ አልፎ በመላው አፍሪካ የሚታወስ ገድል መኾኑን ነው ያነሱት ዶክተር አሰፋ።

የደቡብ ወሎ ዞን ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ አስያ ኢሳ ወሎ የታሪክ እና የባሕል ባለቤት በመኾኑ ሃብቶችን በማልማት እና በማስተዋወቅ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ለመሥራት እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታች ነው ብለዋል።

በዞኑ ያሉ የቱሪዝም ጸጋዎች የዘላቂ ልማት እና እድገት ምንጭ መኾናቸውን ነው የገለጹት። የቱሪዝም ሃብቶችን ማልማት መንከባከብ እና ማስተዋወቅ ከሁሉም ማኅበረሰብ ይጠበቃል ነው ያሉት።

ዘጋቢ፦ ደጀን አምባቸው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article”የአገው ሕዝብ ለሰላም እና ለእድገት ታታሪነቱን አጠናክሮ መቀጠል አለበት” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next article“የአገው ልክ ሰብዓዊነት እና ኢትዮጵያዊነት ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ