”የአገው ሕዝብ ለሰላም እና ለእድገት ታታሪነቱን አጠናክሮ መቀጠል አለበት” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

13

ባሕር ዳር: ጥር 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 86ኛው የአገው ፈረሰኞች በዓል በእንጅባራ እየተከበረ ነው።

በበዓሉ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የአገው ሕዝብ እና ፈረስ ለዘመናት ቁርኝት ያላቸው፣ በባሕል፣ በሰላም እና በልማት የተሳሰሩ እንዲሁም በአደረጃጀት የተቃኙ መኾናቸውን አንስተዋል።

ፈረስ በቀድሞው ጊዜ የሀገር ማስከበሪያ መኾኑ ይታወቃል። ይህንንም ታሪክ በከፍተኛ ኩራት እና አደረጃጀት ጠብቆ ያኖረ ሕዝብ መኾኑን ገልጸው አመስግነዋል።

በማኅበሩ ውስጥ ያሉ ዴሞክራሲያዊ አሠራሮች እና መስተጋብሮችም ለሌላው ሕዝብ አርዓያ እንደሚኾኑ ገልጸዋል።

የአገው ሕዝብ ታታሪ እና ራሱን ከተፈጥሮ ጋር አስማምቶ የሚኖር መኾኑን የገለጹት አቶ አረጋ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ለአየር ንብረት ሚዛን ጥበቃ የተሰጠው ትኩረትንም አድነቀዋል።

የአገው ሕዝብ የሰላምን ፋይዳ ጠንቅቆ የሚገነዘብ፣ ለሰላም የሚተጋ እና ለፍቅር እጁን የሚዘረጋ ሕዝብ ነው። ባለፉት ሁለት ዓመታት ለሰላም መስፈን ያበረከተውን አስተዋጽኦ የሚጠቀስ ነው። ከጽንፈኝነት በመታቀብ እና ጥላቻን በመታገል ጉልህ ሥራ ሠርቷልም ብለዋል።

የአገው ሕዝብ በታሪክ ጠባቂነቱ ብቻ ሳይኾን በሥራ ወዳድነቱ እና ታታሪነቱም ይታወቃል። እደ ጥበብ እና የጎጆ ኢንዱስትሪን በማስፋፋት ለኢንዱስትሪ ማደግ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው። በአጠቃላይም የአዊ ሕዝብ ሁለንተናዊ ስብዕና አርዓያ መኾኑን ነው ርእሰ መሥተዳድሩ የገለጹት።

የአገው ሕዝብ ለመንግሥት የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ተልዕኮዎች ቀናዒ ሕዝብ ነው። ስለኾነም መንግሥት በከፍተኛ አክብሮት ይመለከተዋል። በዓሉን ስናከብርም የሕዝቡን እና የማኅበሩን የቀደመ ታሪክ ተጠንቶ ለዩኔስኮ ለማቅረብ የመጨረሻ ደረጃ በመድረሱ እንኳን ደሥ ያላችሁ ብለዋል።

አቶ አረጋ ከበደ ብሔረሰብ አሥተዳደሩ የሚታወቅባቸውን እሴቶች አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል። ለውስጡ እና ለአካባቢው ሰላም የሚያደርገውን ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል። በደምና አጥንቱ የኢትዮጵያን ታሪክ እንዳቆየ ሁሉ አሁን ደግሞ እውቀቱን እና ጉልበቱን ተጠቅሞ የሀገራችን እና የክልላችን ምጣኔ ሃብት ለማሳደግ የልማት አርበኛ መኾን እንዳለበት አሳስበዋል።

የፈረሰኞች ማኅበር አባላትም አደረጃጀታቸውን በመጠቀም ለሕዝቡ ሰላም፣ ልማት እና አብሮነት እንዲሠሩ ጠይቀዋል።

ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የፈረስ ባሕል የታሪክ ድልድይ እና የፈረስ መስተጋብር የተቆራኘበት ነው” ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው
Next article“መቅደላ አፋፉ ላይ ጩኸት በረከተ የሴቱን አናውቅም ወንድ አንድ ሰው ሞተ”