
ባሕር ዳር: ጥር 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዘመናትን የተሻገረው 86ኛው የአገው ፈረሰኞች በዓል በእንጅባራ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው።
በዓሉ የፌደራል፣ የክልል፣ የዞን እና በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት ሥራ ኀላፊዎች እንዲሁም በዓሉን ለመታደም ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ እንግዶች በተገኙበት ነው በድምቀት እየተከበረ የሚገኘው።
በበዓሉ ላይ ንግግር ያደረጉት የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው በትውልድ ቅብብሎሽ ድር እና ማግ ውስጥ የሚፈጠር አንድ እውነት አለ፤ እሱም ታሪክን ማሻገር የሚችለው እና ድልድይ የኾነው ባሕል ነው ብለዋል። ይህ የፈረስ ባሕል የታሪክ ድልድይ እና የፈረስ መስተጋብር የተቆራኘበት መኾኑን ገልጸዋል።
ፈረስ በአገው ምድር ተራ የእግር አጋዥ ወይም የጭነት ረዳት አይደለም ብለዋል። ይልቁንም የዘመን ተጓዥ እና የታሪክ ምስክር እንደኾነ ገልጸዋል። ፈረስ ለአገው ሕዝብ የማኅበራዊ እሴት ተንቀሳቃሽ እሴት ነው ብለዋል። የአገው ሕዝብ ፈረስን ሁለገብ አርበኛ አድርጎ ሾሞት ይኖራል ነው ያሉት አሥተዳዳሪው።
ፈረስ ከድካም ይልቅ ለውጤት፣ ዘግይቶ ከመድረስ ይልቅ ለቀዳሚነት የታደለ እንደኾነም አንስተዋል። ፈረስ እና የአገው ሕዝብ ቁርኝት በዘመን አጥር የማይታጠር እንደኾነ ነው የገለጹት። ጥንታዊነትን ከዘመናዊነት ጋር አዋድዶ የያዘ ነው ብለዋል።
ይህ ባሕል ዛሬን በደማቁ እያበራ ነገን ለመሻገር በልበ ሙሉነት የሚጓዝ የትውልድ ቅርስ እንደኾነም አቶ ቴዎድሮስ አንስተዋል። ይህ ባሕል በታሪክ የገዘፈ አንጋፋ የሕዝብ ሃብት ነው ብለዋል። ባሕሉ የሚዳሰሱ ባሕላዊ ቅርሶችን እና የማይዳሰሱ መንፈሳዊ እሴቶችን አጣምሮ የያዘ ነው ብለዋል።
የአገው ፈረስ ባሕል ከአገልግሎቱ እና ትርዒቱም በላይ ትልቅ የሰላም ተቋም እንደኾነ ነው የገለጹት። ቅራኔዎች የሚፈቱበት፣ ቁርሾዎች የሚታረቁበት እና የሰላም ቃል ኪዳን የሚታደስበት የፍትሕ ዓደባባይ ነው ብለዋል።
የአገው ፈረስ ባሕልን ልዩ ከሚያደርጉት አውታሮች መካከል በፈረሱ እና በሀገር ህልውና መካከል ያለው ምስጢራዊ ተዛምዶ ነው ብለዋል። መስተጋብሩ ተራ ትርዒት ሳይኾን ኢትዮጵያን የኩራት አክሊል፣ ፈረስን ደግሞ የነጻነት አዕማድ አድርጎ የሳለ ድንቅ የታሪክ ሰነድ ነው ብለዋል። ለዚህም ፈረሰኞች ሲጋልቡ ባንዲራቸውን ከፍ አድርገው እያውለበለቡ መኾኑ ማሳያ እንደኾነ ነው የገለጹት።
አገው ለወል ትርክት ታላቅ አክብሮት ያለው ሕዝብ እንደኾነም ገልጸዋል። ነጠላ ትርክቶች በአገው ሕዝብ አስተሳሰብ ዘንድ ቦታ እንደሌላቸውም አንስተዋል። አገው ነጠላ ትርክትን አያውቅም፤ አያስተጋባምም ነው ያሉት አሥተዳዳሪው። የአገው ሕዝብ ከወንድም ሕዝቦች ጋር በፍቅር ተጋምዶ እና ተዋድዶ የሚኖር የአብሮነት አምባሳደር ነው ብለዋል።
ይህ ታሪካዊ እና አንጋፋ የሕዝብ ባሕል በዓለም አቀፍ ቅርስነት እንዲመዘገብ ጥረቶች እየተደረጉ እንደኾነም አቶ ቴዎድሮስ ገልጸዋል። ይህ መኾኑም ለሀገር ትልቅ ክብር ነው ብለዋል።
ዘጋቢ:- ሰለሞን አንዳርጌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
