
ባሕር ዳር: ጥር 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) እኒያ ጀግኖች ሀገራቸውን በጀግንነት ጠብቀዋል፤ ጸንተው ሀገራቸውን አጽንተዋል፤ ሞተው ሀገራቸውን ሕያው አድርገዋል፤ ደምተው ሀገራቸውን ከጠላት መንጋጋ አውጥተዋል፤ ተከብረው ሀገራቸውን አስከብረዋል።
እኒያ ጀግኖች ለተከበረችው ሠንደቅ ዓላማቸው፤ በነጻነት ለኖረችው ሀገራቸው ክቡር መስዋዕትነት ከፍለዋል። እኒያ ጀግኖች ለኢትዮጵያ ነጻነት፤ ከጥንት ጀምሮ ላልተደፈረው ሉዓላዊነት፤ ለከበረው ኢትዮጵያዊነት ሲሉ በዱር በገደሉ ወድቀዋል፤ በእሾህ እና በአሜካላው ተመላልሰዋል፤ ረሃብ እና ጥሙን ችለዋል፤ መከራውንም ታግሰዋል።
ለኢትዮጵያ ነጻነት፤ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የተዋደቁት ኢትዮጵያውያን ጀግኖች፤ አርበኞች እና እናቶች ብቻ አይደሉም፤ ፈረሶችም ተዋድቀዋል እንጂ።
ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ሀገራቸው ከጠላት ሲከላከሉ የኖሩት፤ በፈረስ እና በበቅሎዎቻቸው፣ እንዲያም ሲል በባዶ እግራቸው እየተጓዙ ነው። ፈረስ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታላቅ አሻራ አለው፤ ፈረስ ያጓጉዛል፤ ፈረስ ስንቅ ያቀብላል፤ ፈረስ ያዋጋል፤ የቆሰለን ያርቃል።
አርበኞች እና ፈረሶች ጥብቅ ቁርጠኝት፣ በጦር ሜዳ የተፈተነ ወዳጅነት አላቸው፤ ጦር ሲወረወር፣ ጎራዴ ከጎራዴ ሲጋጭ፤ ሰይፍ ሲመጣ ፈረሱም አይደነግጥም፤ አርበኛውም አይሸበርም፤ ይልቅስ ፈረሱ አራት እግሩን አንስቶ ወደ ጠላት ሰፈር ይገሰግሳል፤ ጠላቱን እየረገጠ፣ አርበኛው በጎራዴ እንዲሸልተው ያመቻቸዋል እንጂ።
ጀግኖች አርበኞችም በሰጋር ፈረሶቻቸው ላይ ተቀምጠው፤ ጦራቸውን አሹለው፤ ጎራዴያቸውን ስለው፤ ጋሻቸውን አስተካክለው በፈረሶቻቸው ወዲያ እና ወዲህ እየተመላለሱ የኢትዮጵያን ጠላት ይቀላሉ፤ ነፋስ እንደነካው ዱቄት ጠላታቸውን ያበራያሉ።
እንደዛሬው በምድር መሽከርከር፤ በሰማይ መብረር ባልነበረበት ዘመን ፈረስ ያልዘመተበት የኢትዮጵያ አውደ ውጊያ አልነበረም፤ ለዚህም ነው አርበኞች እና ፈረሶች ተባብረው ኢትዮጵያን ጠበቋት የሚባለው።
በፈረስ እየሰገሩ ኢትዮጵያን ካስከበሩ፤ ከእነ ከብሯ ለትውልድ ካሸጋገሩ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች መካከል የአገው ጀግኖች ስማቸው ከፍ ብሎ ይነሳል።
የአገው ጀግኖች ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ጋር በመኾን የኢትዮጵያን ነጻነት አስጠብቀዋል፤ የኢትዮጵያን ጠላቶች ቀጥተዋል፤ ጠላትን አሳፍረዋል፤ አንገት አስደፍተዋል። የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማ በተራራው አናት ላይ ከፍ አድርገው አውለብልበዋል።
“ኢትዮጵያን ለመድፈር ጠላቶች ሲነሱ
እንኳንስ አርበኛው ይቆጣል ፈረሱ” እንደተባለ ኢትዮጵያ ስትነካ የአገው ጀግኖች አርበኞች ብቻ ሳይኾኑ ፈረሱም ይቆጣል፤ ወደ ጠላት ሰፈር ለመገስገስ ያሽካካል፤ በእግሩ ይፎግራል፤ ጀግናውን ይዞ ለመድረስ ይቸኩላል።
የአገው ሕዝብ ለፈረስ የተለየ ፍቅር እና አክብሮት አለው፤ በፈረሱ ክብሩን ይገልጻል፤ በፈረሱ ላይ ኾኖ ማንነቱን ያሳያል፤ ከፍታውን ያስመሰክራል፤ የፈረሱን ውለታም ይዘክራል፤ ለትውልድም ይናገራል።
በዓድዋ አናት ላይ ለሀገሩ ከእነፈረሱ የተዋደቀበትን፤ የጣሊያንን ወረራ ለመመከት የተፋለመበትን፤ ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ሁሉ አንገት ላንገት የተናነቀበትን፤ ተናንቆም ድል ያደረገበትን ታሪኩን ይዘክራል። ከጥንት እስከዛሬ ከፈረስ ጋር ተቆራኝቶ ይኖራል።
እንኳን የሰው ውለታን የፈረሱን ውለታ የማይረሳው የአገው ሕዝብ በፈረሱ ደምቆ በዓል ያከብራል፤ የፈረሱን ውለታ፤ የአርበኞችን አበርክቶ ይናገራል። በአደባባይ ወጥቶ ለዓለሙ ሁሉ ያሳያል። ይህ በዓል የአገው ፈረሰኞች በዓል ይሰኛል።
በዚህ በዓል ፈረሶች ይሸለማሉ፤ ባማረው ማስጌጫ ያጌጣሉ፤ ጀግኖች ፈረሰኞችም ባማረው የክብር ልብስ ይዋባሉ፤ ደምቀው ይታያሉ፤ እናቶች፣ ወይዛዝርቱ እና ጎበዛዝቱ ልብን በሚያስደነግጥ ግርማ ይወጣሉ። ቀልብን በሚስብ ውበት ይታያሉ፤ ጀግኖቹ ባማረው ፈረሳቸው ላይ ተቀምጠው በኩራት እና በክብር ይመላለሳሉ፤ ከፈረሶቻቸው ጋር ያላቸውን ወዳጅነት ይገልጣሉ።
የአገው ጀግኖች ባማረው እና በተዋበው ባሕላቸው አጊጠው፤ በፈረሶቻቸው ላይ ተቀምጠው ሲወጡ ያቺ ከጥንት ጀምሮ የተዋደቁላትን፤ ለክብሯ የሞቱላትን፤ ለፍቅሯ መስዋዕትነት የተቀበሉባትን፤ መከራውን የቻሉባትን አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀዩዋን ሠንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው ያውለበልቧታል፤ እርሷን ከፍ ሳያደርጉ አይወጡም፤ እርሷን ሳይዙ አያጌጡም፤ ፈረስ ከተሸለመ ሠንደቋም አብራ ትወጣለች፤ በፈረሱ አናት ላይ ትውለበለባለች።
ሰው በልቶ የጠገበ የማይመስላቸው የአገው እናቶች አሳምረው የሠሩትን ምግብ ያቀርባሉ፤ ከጋኑ እየጠለቁ፣ ከገንቦው እያዘነበሉ ጠላውን ይቀዳሉ፤ ጠጁን ያንቆረቁራሉ፤ ስሞት አፈር ስኾን (ድባንጃስ ኹዋቲኑማ ናና ቹትካ) እያሉ ያበላሉ ያጠጣሉ፤ እንግዳን በከበረው ሥፍራ አስቀምጠው ያቀማጥላሉ። ያን ጊዜ ደስታ እና ተድላ ይኾናል፤ ያን ጊዜ ክብር ሲንጎማለል ይታያል።
ይህ በዓል አንድነት የሚገለጽበት፤ ደግነት የሚንጸባረቅበት፣ ጀግንነት የሚታይበት፣ ኅብረት የሚጠነክርበት፤ ውለታ የሚነገርበት፤ ትናንት፣ ዛሬ እና ነገ የሚተሳሰርበት፤ የሀገር ባለውለታዎች የሚዘከሩበት፤ ለሀገር አንድነት እና ክብር የሚመከርበት፤ የኢትዮጵያዊነት መልክ የሚገለጥበት ድንቅ በዓል ነው።
በአገው ፈረሰኞች በዓል ጀግኖች ይዘከራሉ፤ ፈረሶች ይከበራሉ፤ በዚህ በዓል የጥንቱ ባሕል ከእነ ክብሩ፣ ከእነ ማዕረጉ ይገለጣል፤ በዚህ በዓል እሴት እና ማንነት ይደምቃል።
እነኾ በዓሉ ዛሬ ነውና የአገው ጀግኖች ደምቀዋል፤ የአገው እናቶች አሸብርቀዋል፤ ወይዛዝርቱ እና ጎበዛዝቱ በግርማ ወጥተዋል።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
