
አዲስ አበባ: ጥር 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “አዲስ አበባ የባሕል እና ፈጠራ ሞዛይክ” በሚል መሪ መልዕክት ፌስቲቫሉ እየተከበረ ነው።
የአዲስ አበባ ባሕል፣ ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ ሂሩት ካሳው (ዶ.ር) አዲስ አበባ ቅርሶቿን ተንከባክባ፣ ጠብቃ እና አድሳ ለትውልድ እያስተላለፈች ትገኛለች ብለዋል።
ባሕል ምን ያህል የሀገር ምሰሶ እና ሃብት መኾኑን ሁሉም ይገነዘባል ነው ያሉት ዶ.ር ሂሩት።
አዲስ አበባ ለፈጠራ በሚተጉ ልጆቿ የፈጠራ መነኸሪያም ኾና እየደመቀች ወደ ብልጽግና እየተስፈነጠረች መኾኗንም ተናግረዋል።
አዲስ አበባ ይህንን የባሕል፣ የጥበብ እና የፈጠራ ሞዛይክነቷን ይዛ ለኢትዮጵያ ዕድገት አስተዋጽኦ ማድረጓን ትቀጥላለች ብለዋል።
ከተማዋ ብዝኀ ቤትነቷን ጠብቃ እየተጓዘች ያለች ከተማ ናት ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ ናቸው።
አዲስ አበባ የባሕልን ጠንካራ ምሰሶነት ያሳየች፣ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይኾን የአፍሪካ እና የዓለም ሕዝቦች የትኩረት ማዕከል የኾነች ከተማ ናት ብለዋል አቶ ጃንጥራር።
የከተማ ቱሪዝም እንቅስቃሴ በአዲስ አበባ በከፍተኛ ዕድገት ላይ ያለ ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው ከአድዋ ሙዚየም እስከ አዲስ አፍሪካ ኮንቬንሽን ማዕከል የተሠሩ ሥራዎች የከተማዋን የኮንፈረንስ ቱሪዝም መዳረሻነት ዕውን መኾን የሚያረጋግጡ ናቸው ብለዋል።
የባሕል ልማት እና የፈጠራ ሥራን ማበረታታት እና ምቹ ሁኔታ መፍጠር የከተማዋ ተቀዳሚ ተግባር መኾኑንም አቶ ጃንጥራር ጠቁመዋል።
በኤግዚቢሽን ማዕከል በተከፈተው 17ኛው ከተማ አቀፍ ፌስቲቫል የባሕል እና የፈጠራ ሥራ ውጤቶች ለዕይታ በቅተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
