”ከልክ በላይ በፍጥነት ማሽከርከር ፈጥኖ አያደርስም” ዓለሙ ስሜ (ዶ.ር)

12

ባሕር ዳር: ጥር 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚንስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ.ር) በአማራ ክልል ባሕር ዳር ከተማ ጎጃም በር የአውቶቡስ መናኸሪያ ተገኝተው ለአሽከርካሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ሰጥተዋል።

ሚንስትሩ እየጨመረ ስለመጣው የትራፊክ አደጋ ለአሽከርካሪዎች አስገንዝበዋል። የኢትዮጵያ የተሽከርካሪ ብዛት ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነጻጸር በቁጥር ጥቂት ቢኾንም የሚያደርሰው አደጋ ግን ብዙ መኾኑን ጠቁመዋል።

የትራፊክ አደጋ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱንንም ጠቁመዋል። ይህንን ችግር ለመቀነስ ግንዛቤ የመፍጠር ንቅናቄ መጀመሩን ነው የገለጹት። አደጋዎችን በመቀነሱ ረገድ የአሽከርካሪዎች ድርሻ ከፍተኛ መኾኑንም ነው የጠቆሙት።

ግንዛቤ ፈጠራው በሀገር ደረጃ እየተሠራ መኾኑን ገልጸው አሽከርካሪዎችን ባሉበት ሁሉ እያገኙ የችግሩን መንስኤ በስፋት ማስተማር እንደሚቀጥልም ነው የተናገሩት።

”ከልክ በላይ በፍጥነት ማሽከርከር ፈጥኖ አያደርስም” ያሉት ሚንስትሩ በተመጠነ የፍጥነት ልክ እና ሕጉን አክብሮ ማሽከርከር ከአደጋ እንደሚያድን ተናግረዋል፡፡

የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ደረጃው ቢለያይም ሁሉም ድርሻ እንዳለው ሚንስትሩ ገልጸዋል። አሽከርካሪዎች ትልቅ ኀላፊነት ስላለባቸው በዕውቀት፣ በክህሎት እና በኀላፊነት ማሽከርከር እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል። ሌሎች ባለድርሻ አካላትም መጠንቀቅ እና ኀላፊነታቸውን መወጣት እንደሚገባቸው ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ታሪክ እየተቀየረ ነው፤ በትራፊክ ደኅንነትም በኩል ያለውን የከፋ አደጋ ታሪክ መቀየር አለብን ያሉት ዶክተር ዓለሙ ስሜ አሽከርካሪዎች ለራሳቸው፣ ለቤተሰባቸው እና ለሕዝባቸው ሲሉ በጥንቃቄ እንዲያሽከረክሩም አደራ ብለዋል።

የአማራ ክልል መንገድ፣ ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ቢሮ ኀላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ.ር) በክልሉ በየዓመቱ የሚደርሰው የትራፊክ አደጋ በሺህ የሚቆጠር መኾኑን ገልጸዋል። በዚህም የሕይወት እና የንብረት ውድመት እንደሚደርስ ነው የተናገሩት። ችግሩን ለመቀነስ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።

አብዛኛው የአደጋዎች መንስኤ የአሽከርካሪዎች የጥንቃቄ ጉድለት መኾኑ በጥናት ተረጋግጧል ነው ያሉት። ስለኾነም በአሽከርካሪዎች እና ማኅበረሰቡ ላይ ሥራ የመሥራትን አስፈላጊነት ተናግረዋል።

የፌዴራል ከፍተኛ ባለሥልጣናትም በባሕር ዳር መናኸሪያ ተገኝተው የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መሥራታቸውን ገልጸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው የገለጹት። ለዚህ ሥራም መገናኛ ብዙኀን ጭምር እንዲተባበሩ ጠይቀዋል።

አርቲስት ጊዮን ዓለምሰገድ በቦታው ተገኝቶ ባስተላለፈው መልዕክት አሽከርካሪዎች በሰላም ወጥተው በሰላም እንዲገቡ ተረጋግተው እና አስተውለው የማሽከርከርን አስፈላጊነት ገልጿል። ብቁ ሥልጠና ሳይወስዱ በሚያሽከረክሩ ሹፌሮችም የአደጋው ምክንያቶች ስለኾኑ ከአደጋው ሊጠነቀቁ እንደሚገባ አሳስቧል።

ሹፌር ከድር ኢብራሒም ተጠንቅቆ እንደሚያሽከረክሩ ገልጸውልናል። በዚህም ለ21 ዓመት ሲያሽከረክሩ አደጋ ገጥሟቸው እንደማያውቅ ተናግረዋል። የመንገድ እና የተሽከርካሪ ብዛት አለመጣጣም፣ በየቦታው ያለው ኬላን ለማለፍ የሚደረግ ፍጥነትም ለአደጋ እያጋለጠ መኾኑን ጠቁመዋል።

ሾፌሮች በጥንቃቄ እና በኃላፊነት ማሽከርከር ይገባናልም ነው ያሉት።

ሹፌር ውበቴ ዓለማየሁ በበኩላቸው ለትራፊክ አደጋ አንዱ መንስኤ በአንድ ጊዜ የሚሰጥ ከፍተኛ የማሽከርከር ፈቃድ፣ የተሽከርካሪዎች ዘመናዊነት እና በመነኻሪያ ውስጥ የስምሪት አሰጣጥ ጉድለቶች እንዳሉ አንስቷል።

አደጋውን ለመቀነስ ማስተማር እና ማብቃት ላይ ተጠናክሮ መሠራት እንዳለበትም ገልጿል።

ዘጋቢ ፡- ዋሴ ባየ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአገው ፈረስ ባሕል እና በሀገረሰባዊ ጥበባት ላይ ትኩረት ያደረገ ሲምፖዚዬም እየተካሄደ ነው።
Next articleየባሕል ልማት እና የፈጠራ ሥራን ማበረታታት እና ምቹ ሁኔታ መፍጠር የከተማዋ ተቀዳሚ ተግባር ነው።