የሠራተኞች ፍልሰት ሕጋዊ እና ሥርዓት ያለው እንዲኾን ክልላዊ ትብብርን ማጠናከር ይገባል።

8
አዲስ አበባ፡ ጥር 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ)
ዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት ከአውሮፓ ኅብረት ጋር በመተባበር የሠራተኞች ከሀገር ውጭ ፍልሰትን አስመልክቶ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምሥራቅ፣ የፓስፊክ እና የእስያ ዳይሬክተር አምባሳደር ዳዋኖ ከድር ኢትዮጵያ ሕጋዊ የውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪትን ዜጋ ተኮር በኾነው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ቁልፍ ተግባር አድርጋ እየከወነች ትገኛለች ብለዋል።
በተለይም ከመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ጋር በሠራተኞች ደኅንነት እና መብት መጠበቅ በተደረጉ ስምምነቶች ስኬታማ ሥራዎች ስለመሠራታቸው አስረድተዋል።
ነገር ግን አሁንም ሕገ ወጥ ስደት አንገብጋቢ ችግር ኾኖ ቀጥሏል ነው ያሉት። በተለይም ተግባራት በተበታተነ መልኩ መፈፀማቸው ችግሩን የተወሳሰበ እንዳደረገው ተጠቁሟል። ችግሩን በትብብር ለመፍታት ኢትዮጵያ ቁርጠኛ ነችም ነው ያሉት።
በመድረኩ የተገኙት የዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ንዳባ ኩምቡላ ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ፖሊሲ እና አሠራሮችን በማውጣት ሕጋዊ የውጭ ሀገራት የሠራተኞች ስምሪት እየሰጠች እንደምትገኝ ተናግረዋል።
በዚህ ሕጋዊ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የውጭ ሀገራት የሠራተኞች ስምሪት የሠራተኞችን ደኅንነት፣ መብት እና ጥቅም ማስጠበቅ ተችሏል ነው ያሉት።
ይህን ጅምር ይበልጥ ስኬታማ ለማድረግ ተግዳሮቶችን በቅንጅታዊ አሠራር መፍታት እንደሚገባም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ ተወካይ ሉቡሜራ ሜሬስቫ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት በሕጋዊ መንገድ የውጭ ሀገራት የሠራተኞች ጉዞ ማካሄድ የሚያስችል አሥተዳደርን በማጠናከር፣ አስፈላጊ ማሻሻያዎችን በማድረግ ብሎም ተቋማዊ አወቃቀሮችን እና የፖሊሲ ቁርጠኝነትን በማጎልበት በኩል ላሳየችው ቁርጠኝነት ዕውቅና መስጠት እንፈልጋለን ብለዋል።
ኅብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ባከናዎናቸው በርካታ ተግባራት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል ነው ያሉት። አሁንም ግን ሕገ ወጥ ስደት አንገብጋቢ በኾነ መልኩ በመስፋፋቱ ይህን ችግር ለመቅረፍ ቀጣናዊ ትብብርን ማጠናከር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ለዚህ መርሐግብር ስኬትም ኅብረቱ የገንዘብ እና ሌሎች ድጋፎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
በውይይት መድረኩ ለቀጣይ ተግባራት ስኬት አቅጣጫ እንደሚቀመጥም ተመላክቷል።
ዘጋቢ፦ ኢብራሂም ሙሃመድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበትንሽ ቦታ ላይ መለወጥ ይቻላል።
Next articleበአገው ፈረስ ባሕል እና በሀገረሰባዊ ጥበባት ላይ ትኩረት ያደረገ ሲምፖዚዬም እየተካሄደ ነው።