በትንሽ ቦታ ላይ መለወጥ ይቻላል።

9
ፍኖተ ሰላም: ጥር 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት ስድስት ወራት ከ32 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩን የምዕራብ ጎጃም ዞን ሥራ እና ክህሎት መምሪያ አስታውቋል።
ገበያው፣ አምደ ወርቅ እና ጓደኞቹ ሽርክና ማኅበር በቡሬ ከተማ በዕደ ጥበብ ሥራ እና በቀንድ ፕላስቲክ ውጤቶች ዘርፍ የተሠማራ ማኀበር ነው።
ከ40 ሺህ ብር ባልበለጠ ካፒታል ሥራቸውን የጀመሩት ወጣቶቹ አሁን ላይ ከራሳቸው አልፈው ለ10 ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውንም የማኅበሩ ሠብሣቢ ገበያው አንለይ ተናግሯል። በቀን እስከ 200 የፕላስቲክ ዋንጫዎችን እንደሚያመርቱም ገልጾልናል።
አማረ፣ ወርቅነሽ እና ጓደኞቹ ሽርክና ማኅበር ደግሞ በቡሬ ከተማ በዶሮ እርባታ የሥራ ዘርፍ ተሠማርተው እየሠሩ ነው። በ20 የእንቁላል ደሮዎች ሥራቸውን የጀመሩት ሥራ ፈጣሪዎች አሁን ላይ ከ2 ሺህ 800 በላይ ደርሰዋል። በቀንም እስከ 1 ሺህ 800 እንቁላሎች እንደሚያገኙ የማኅበሩ አባል አማረ አገኘሁ ተናግሯል።
ከመንግሥት ሥራ በመውጣት ወደ ዘርፉ እንደገቡ የገለጸው ሥራ ፈጣሪው መሥራት ከተቻለ በትንሽ ቦታ ላይ መለወጥ እንሚቻል ገልጿል። እንቁላል ከከተማው አልፈው ወደ ሌሎች አካባቢዎች እያቀረቡ መኾናቸውን ተናግሯል።
አሁን ላይ አጠቃላይ ካፒታላቸው እስከ 2 ሚሊዮን በላይ ብር መድረሱንም አንስቷል። ከእንቁላል ደሮ እርባታ በተጨማሪ የዶሮ መኖ ማቀነባበር መጀመራቸውንም ነው የተናገረው።
የቡሬ ከተማ አሥተዳደር ሥራ እና ክህሎት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ወርቁ በሪሁን በበጀት ዓመቱ 7 ሺህ 823 ለሚኾኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱን ገልጸዋል። ባለፉት ስድስት ወራት በተለያዩ ዘርፎች ከ4 ሺህ 700 በላይ ወጣቶች ተጠቃሚ መኾናቸውንም ጠቁመዋል።
በሥራ ፈጣሪዎች ላይ የሚያጋጥሙ የፋይናንስ እና የቦታ ተግዳሮቶችን ለመፍታት በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ በዞኑ ለ64 ሺህ 895 ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ እየተሠራ መኾኑንም የምዕራብ ጎጃም ዞን ሥራ እና ክህሎት መምሪያ ኀላፊ አያሌው ያረጋል ገልጸዋል። እስካሁንም በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ለ32 ሺህ 951 ወጣቶች ጊዚያዊ እና ቋሚ የሥራ ዕድል መፈጠሩምን ተናግረዋል።
የሥራ ዕድል ተጠቃሚዎችን ውጤታማ ለማድረግ የቦታ ማስፋፊያ እና የፋይናንስ አቅርቦት ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል። በዚህም በበጀት ዓመቱ 191 ሚሊዮን ብር ብድር መሠራጨቱን ጠቅሰዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበትንሽ ቦታ ላይ መለወጥ ይቻላል።
Next articleየሠራተኞች ፍልሰት ሕጋዊ እና ሥርዓት ያለው እንዲኾን ክልላዊ ትብብርን ማጠናከር ይገባል።