
ደሴ፡ ጥር 22/2018ዓ.ም (አሚኮ) የ2018 ዓ.ም የአንደኛው ወሰነ ትምህርት ተጠናቅቋል። የ1ኛው ወሰነ ትምህርት መጠናቀቁን ተከትሎ የተማሪዎችን የእረፍት ጊዜ አጠቃቀም በተመለከተ በደሴ ከተማ የሆጤ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና የእቴጌ መነን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን፣ ወላጆችን እና መምህራንን አሚኮ አነጋግሯል።
የ11ኛ ክፍል ተማሪ ማህደር ታምራት፣ ዮርዳኖስ መካሻ እና የ12ኛ ክፍል ተማሪ አብዱልአዚዝ ዘገየ የእረፍት ጊዜያቸውን ከመዝናኛነት ባለፈ በተጠናቀቀው የ1ኛው ወሰነ ትምህርት ላይ ባመጡት ውጤት መነሻነት በቀጣዩ ወሰነ ትምህርት ይበልጥ ለማሻሻል የሚዘጋጁበት እንደኾነ ተናግረዋል።
ወላጆች ግን በተለይ በ1ኛ ደረጃ ትምህር ቤት ላይ ያሉ ልጆቻቸው በአብዛኛው በመዝናናት እና በጨዋታ እንዲያሳልፉት ማሰባቸውን ገልጸዋል።
ተማሪዎች በ1ኛው መንፈቅ ዓመት ያገኙትን ውጤት ይበልጥ ለማሻሻል ዝግጅት የሚያደርጉበት መኾን እንዳለበት ደግሞ የእቴጌ መነን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር አብዱ ይማም እና የሆጤ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእስ መምህር ጌታቸው መከተ ገልጸዋል።
ውጤታቸውን ገምግመው የተሳሳቱትን የሚያርሙበት የሚኒስትሪ እና የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ተፈታኞች ደግሞ ያለፏቸውን የክፍል ደረጃዎች መለስ ብለው የሚያዩበት እና ቤተ መጻሕፍትን የሚጎበኙበት ሊኾን እንደሚገባ ተናግረዋል።
ወላጆች ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ ያሉ ልጆችን የእረፍት ጊዜን ያለ ጫና ለ2ኛው ወሰነ ትምህርት የሚዘጋጁበትን ስልት መቀየስ እንዳለባቸው በደሴ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የአካዳሚክ ጉዳዮች ዲን እና የሥነልቦና መምህርት መንበረ ላቀው አመላክተዋል።
በእረፍት ጊዜያቸው ልጆች እየተዝናኑ የሚማሩባቸውን ቪድዮዎችን፣ ጌሞችን እና መጻሕፍትን በወላጆች እገዛ በፕሮግራም መጠቀም እና ቀጣዩን የትምህርት ዘመን በጉጉት እንዲጠብቁ ያለ ጫና ክትትል እና ድጋፍ መስጠት ተገቢ መኾኑን አስገንዝበዋል።
የ8ኛ እና የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የሚፈተኑ ተማሪዎች ደግሞ ያለፏቸውን የክፍል ደረጃዎች ተመልሰው የሚያዩበት በመኾኑ ከመጻሕፍት በተጨማሪ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የተመረጡ የቪዲዬ ትምህርቶችን በመጫን፣ የኦንላይን አጋዥ ትምህርቶችን በመከታተል እንዲጠቀሙ ማገዝ ከወላጆች የሚጠበቅ መኾኑን የሥነ ልቦና መምህርቷ መንበረ ላቀው ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- መሃመድ በቀለ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
