
ባሕር ዳር፡ ጥር 22/2018ዓ.ም (አሚኮ) ለአገው ሕዝብ መገለጫ፣ የታሪክ አሻራ የኾነው የአገው የፈረሰኞች በዓል ጥር 23/2018 ዓ.ም በእንጅባራ ከተማ ይከበራል።
በእንጅባራ ከተማ የሚገኙ ሆቴሎች እና የአገልግሎት ሰጭ ተቋማትም ዝግጅታቸውን አጠናቅቀው እንግዶችን እየተቀበሉ ነው።
የግሬስ ሆቴል ባለቤት መላከ ሰላም ግርማ እጅጉ እንደገለጹት የአገው ፈረስ በዓልን ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል በቂ ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ሆቴሎቹ ዛሬም እንግዶችን እየተቀበሉ እና እያስተናገዱ እንደሚገኙ ነው የገለጹት።
ጊዜያዊ ጥቅምን እና ዛሬን ብቻ ሳይኾን ነገን አስበን ለእንግዶች አገልግሎት እየሰጠን ነው ብለዋል። በጥራትም፣ በአቅርቦትም፣ በዋጋም ተመጣጣኝ የኾነ አገልግሎት እየሰጡ መኾኑንም ጠቁመዋል።
የእሱቤ ገበታ ባለቤት እሱባለው መስፍን የሚመጡ እንግዶችን “አዲናስ” በማለት እየተቀበልን ጥሩ ጊዜ እንዲያሳልፉ አስበን እያስተናገድን ነው ብለዋል። ጥራት እንጂ ዋጋ አንጨምርም ብለው በመወሰን የተሻለ አገልግሎት እያቀረቡ እንደሚገኙም ገልጸዋል። ቀድሞ ከነበረው ምንም ዓይነት ዋጋ እንዳልተጨመረም ተናግረዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ተተኪ ኀላፊ ወለሊ ጌቴ እንግዶች በቆይታቸው ጥሩ ጊዜ እንዲያሳልፋ ከአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ጋር ውይይት ተደርጎ ሰፊ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱንም ገልጸዋል።
ሆቴሎችም በራሳቸው አደረጃጀት ተወያይተው የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ማድረጋቸውን አንስተዋል። ሌሎች አደረጃጀቶችን በመጠቀምም እንግዶች በቆይታቸው ጥሩ መስተንግዶ እንዲያገኙ በቂ ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
