
ባሕር ዳር: ጥር 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከተማ ልማት ዘርፍ የስድስት ወራት የዕቅድ አፈጻጸሙን እየገመገመ ነው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አሥተባባሪ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) ተቋማቱ ባለፉት ስድስት ወራት የክልሉን ሕዝብ ተጠቃሚነት ከፍ የሚያደርጉ ሥራዎችን ሲያከናውኑ መቆየታቸው አንስተዋል።
በክልሉ እና በፌዴራል መንግሥት የተያዙ ፕሮጀክቶች በልዩ ተነሳሽነት እየተፈጸሙ መኾኑን ተናግረዋል። እነዚህ ፕሮጀክቶች በዋናነት የዜጎችን ገቢ ከማሳደግ፣ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ከማስፋፋት እና ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ከማድረግ አኳያ እየተከናወኑ የሚገኙ መኾናቸውን ጠቁመዋል።
የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ በመንግሥት እና በፓርቲ በኩል ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው፤ በተለይም ምርቶች በብዛት እና በጥራት ለሕዝቡ እንዲቀርቡ የክልሉ ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ከሌሎችም የሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመቀናጀት ውጤታማ ሥራዎችን አከናውኗል ብለዋል።
የገበያ ማዕከላት በየከተማው መቋቋማቸው እና በኑሮ ላይ ጫና የሚፈጥሩ ሕገ ወጥ ኬላዎች መነሳታቸውም የምርቶችን ዋጋ ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀነስ አስችሏል ነው ያሉት።
በየመንገዱ ኬላ እየዘረጉ መኪና ባለፈ ቁጥር ገንዘብ የሚጠየቅበት ሕገ ወጥ አሠራር በዚህ ዓመት ሙሉ በሙሉ እንዲቀረፍም ግብረ ኀይል ተቋቁሞ የቁጥጥር እና ክትትል ሥራ እየተከናወነ መኾኑን አስታውቀዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት 36 ሺህ በላይ አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች ተቋቁመው 626 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ማግኘታቸውንም ተናግረዋል።
በክልሉ ከተሞች አየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማትም ለ77 ሺህ ዜጎች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።
ከኮሪደር ልማት ጋር ተያይዞ ዘመናዊ ከተሞች እና ሰው ተኮር መሠረተ ልማቶች እየተገነቡ መኾናቸውን ጠቁመዋል።
በሁሉም የክልሉ ዞኖች የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች እንዲለሙ ግብ ተይዞ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
የመኖሪያ ቤት ችግሮችን ለማቃለል የሚያስችሉ በርካታ ቤቶችን ለመገንባትም የሕግ ማዕቀፎች ተዘጋጅተዋል ነው ያሉት።
አምራች ኢንዱስትሪው በዕድገት ውስጥ ያለውን ድርሻ ወደ ሁለት ዲጂት ለማድረስ ግብ ተይዞ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። ከፍ ያለ ውጤት እንደሚገኝ የሚያመላክቱ ሥራዎችም ተከናውነዋል ብለዋል። በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ችግሮችን በመፍታት 85 አምራች ኢንዱስትሪዎች በአዲስ ወደምርት መግባታቸውን አንስተዋል። ምርት አቋርጠው የነበሩ ነባር 35 ኢንዱስትሪዎችንም ወደማምረት መልሰናል ብለዋል።
ዲጂታል ኢትዮጵያን በክልሉ ሊያሳካ የሚችል የኢትዮ ኮደርስ ሥልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። በተለይም ባለፉት ስድስት ወራት በርካታ ወጣቶች ሥልጠናውን መውሰዳቸውን ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
