
ደብረ ማርቆስ: ጥር 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ)የምሥራቅ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አሠራሩን ዲጂታላይዝድ እያደረገ መኾኑን አስታውቋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ባየ ጌታቸው ኢ-ፋይሊንግ እና ዲጂታል መዝገብ መጀመሩ የፍርድ ሂደቱን ቀልጣፋ እና ግልጽ አድርጎታል ብለዋል። ተጠቃሚዎችም አገልግሎቱን በቀላሉ እያገኙ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ዲጂታል ሥርዓቶች የፍርድ ሂደትን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ሙስናን ለመቀነስ እና የሕዝብ እምነትን ለማጠናከር ያግዛሉ ነው ያሉት።
የፍትሕ ሥርዓቱን ዘመናዊ ለማድረግ የተጀመሩ የዲጂታል ለውጦች የፍርድ ሂደቶችን ፍጥነት፣ ግልፅነት እና ተደራሽነት ለማሻሻል አስፈላጊ እርምጃ መኾናቸውን ገልጸዋል።
በአዲሱ የዲጂታል ሥርዓት መሠረት የክስ መዝገቦች ከወረቀት ወደ ኤሌክትሮኒክስ መዝገብ ተቀይረው መመዝገብ ጀምረዋል፤ ይህም የፍርድ ቀጠሮ መዘግየትን ለመቀነስ እና የፋይል መጥፋት ችግሮችን ለመከላከል ጠቃሚ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የደብረ ማርቆስ ምድብ ችሎት አስተባባሪ መኮንን ደምለው ከዚህ በፊት የተለያዩ ፋይሎችን ለማግኘት ብዙ ቀናት ይወስድ እንደነበር ገልጸዋል። አሁን ላይ ግን አገልግሎቱ ዲጂታላይዝ መደረጉ ፋይሎችን በአጭር ጊዜ እና ጉልበት ቆጣቢ በኾነ መልኩ በኮምፒዩተር ውስጥ በፍጥነት ማግኘት እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።
አገልግሎቱ የሥራ ጥራትንም የሚጨምር እና የደንበኞችን እንግልትም የሚቀንስ እንደኾነም ተናግረዋል።
የፍትሕ ሥርዓቱን ዲጂታል ማድረግ ፍርድን ፈጣን፣ ግልፅ እና ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ አስፈላጊ እርምጃ መኾኑን ገልጸዋል።
የፍርድ ቤት ደንበኞችም ረዥም ርቀት ተጉዘን ጉዳይ እናቀርብ ነበር፤ አሁን ግን ፕላዝማ በመጠቀም ጉዳያችንን በቅርበት መከታተል ችለናል ነው ያሉት።
በአዲሱ የዲጂታል ሥርዓት መሠረት የክስ መዝገቦች ከወረቀት ወደ ኤሌክትሮኒክስ የመቀየር ሂደት እና ዘመናዊ የፍትሕ ሥርዓት መገንባትን ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑም ተመላክቷል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
