
ባሕር ዳር: ጥር 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የገጠር ልማት ክላስተር በሥሩ ከሚገኙ ተቋማት ጋር በግማሽ ዓመቱ በተከናወኑ ዋና ዋና ሥራዎች ላይ ውይይት አድርጓል።
በበጀት ዓመቱ በከልሉ የ25 ዓመት የአሻጋሪ ዕድገት እና የዘላቂ ልማት ፍኖተ ካርታ፣ የአምስት ዓመት ስትራቴጅከ ዕቅድ እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱ ይታወሳል።
በ2018 በጀት ዓመት አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገቱን በ2017 በጀት ዓመት ከነበረበት 6 ነጥብ 8 በመቶ ወደ 9 ነጥብ 5 በመቶ ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑን
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ገልጸዋል። የግብርናውን ዘርፍ ዕድገት ደግሞ ከነበረበት 4 ነጥብ 9 በመቶ ወደ 8 ነጥብ 6 በመቶ ለማሳደግ ግብ ተይዞ እየተሠራ መኾኑንም አስረድተዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት የተሠሩ ዋና ዋና ሥራዎችንም አብራርተዋል። በዚህ ዓመት በግዥ ከተፈጸመው 8 ሚሊዮን 640 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ እስካሁን ከ1 ሚሊዮን 435 ሺህ ኩንታል በላይ የሚኾነው ጅቡቲ ወደብ ላይ መድረሱን ነው የገለጹት። 339 ሺህ ኩንታሉ የሚኾነው ደግሞ ወደ አርሶ አደሩ ተሰራጭቷል።
494 ትራክተር ለአርሶ አደሮች መሠራጨቱን የገለጹት አሥተባባሪው ከ1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ደግሞ በትራክተር ታርሷል ብለዋል።
318 ሺህ ሄክታር መሬት ደግሞ በበጋ መስኖ ስንዴ ማልማት መቻሉን ገልጸዋል። አርሶ አደሮች የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር አስይዘው የብድር ተጠቃሚ እንዲኾኑ ማድረግም ተችሏል ነው ያሉት። በማዕድን ዘርፍም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የተገኘበት ወቅት መኾኑን ገልጸዋል።
ሁለገብ ኅብረት ሥራ ማኅበራትን የማዘመን ሥራ መሠራቱንም ነው የተናገሩት። ጥብቅ ደኖች እና ብሔራዊ ፓርኮች ጉዳት እንዳይደርስባቸው የክትትል ሥራ መሠራቱንም አብራርተዋል።
ይሁን እንጅ ክልሉ ያለውን የመልማት አቅም ታሳቢ ያደረገ ዕቅድ አቅዶ ወደ ሥራ የመግባት ችግር መኖሩንም ገልጸዋል። በቀጣይ የክልሉን ምጣኔ ሃብት ሊያነቃቃ የሚያስችል ንቅናቄ መፍጠር ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መኾኑንም አስረድተዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
