የጅጋ_ቋሪት_አርብ ገበያ ሎት አንድ የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክት ምን ላይ ነው?

6
ፍኖተሰላም: ጥር 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጅጋ_ቋሪት_አርብ ገበያ ሎት አንድ 59 ኪ.ሜ የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክት ወደ ሥራ የገባው በ2013 ዓ.ም ነው።
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ምዕራብ ጎጃምን ከሰሜን ጎጃም እና አዊ ዞኖች ጋር በማገናኘት ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮችን የሚያሳልጥ ሁነኛ መንገድ ነው። መንገዱ በሦሥት ዓመታት ይጠናቀቃል ተብሎ ወደ ሥራ ቢገባም በተያዘለት ጊዜ ባለመከናወኑ በአካባቢው ኅብረተሰብ ዘንድ ቅሬታን ፈጥሯል።
የቋሪት ወረዳ ነዋሪ ክብረት ሙሉነህ እና ስንታየሁ ፈንቴ አስፋልት መንገዱ ለበርካታ ጊዜ በኅብረተሰቡ ዘንድ ሲጠየቅ የነበረ ፕሮጀክት መኾኑን ተናግረዋል።
አስፋልት መንገዱ ሲጠናቀቅ በአርብ ገበያ እና አዴት በማድረግ ወደ ባሕር ዳር ለመጓጓዝ ከፍተኛ ጫናን እንደሚቀንስላቸው ነው የተናገሩት።
ይሁን እንጅ አስፋልት መንገዱ በተያዘለት ጊዜ ባለመከናወኑ እየተቸገሩ መኾኑን ተናግረዋል።
ለአስፋልት መንገዱ ተብሎ የተጀመረው የመንገድ ጠረጋ ሥራም መቋረጡን አስረድተዋል። በመኾኑም ፕሮጀክቱ በፍጥነት እንዲከናወንላቸው ጠይቀዋል።
የጅጋ_ቋሪት_አርብ ገበያ ሎት አንድ አስፋልት መንገድ ፕሮጀክት ተወካይ ሥራ አሥኪያጅ አዳሙ ጌትነት ፕሮጀክቱን በሚፈለገው ልክ ለማከናወን የጸጥታ ችግሩ ከፍተኛ ተግዳሮት መፍጠሩን ጠቁመዋል።
በተለይ በጸጥታ ችግሩ ሳቢያ ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልጉ ማሽኖችን ለማቅረብ ባለሃብቶች ፈቃደኛ አለመኾናቸውንም ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ በሚሠራባቸው አካባቢዎች ከሦሥተኛ ወገን ነፃ ያልኾኑ መሬቶች በመኖራቸው እንቅፋት መፍጠሩንም አንስተዋል።
የቋሪት ወረዳ አሥተዳደር ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ላስብ ካሳሁን የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክቱ መንግሥት የኅብረተሰቡን የረጅም ጊዜ የልማት ጥያቄ የመለሰበት መኾኑን ገልጸዋል።
ተቋራጩ ለፕሮጀክቱ በቂ የሚኾን ግብዓት ባለማቅረቡ እና በሙሉ አቅም ወደ ሥራ ባለመግባቱ ፕሮጀክቱ መዘግየቱን አስረድተዋል።
ቦታውን ከሦሥተኛ ወገን ነፃ ለማድረግ ለበርካታ አርሶአደሮች የካሳ ክፍያ መፈፀሙንም ተናግረዋል። ቀጣይ ከሦሥተኛ ወገን ነፃ ያልኾኑ አካባቢዎችን ነፃ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
በኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የቡሬ እና አካባቢው ፕሮጀክት ሥራ አሥኪያጅ ሁሉ አለምነህ ፕሮጀክቱ አሁን ላይ 38 በመቶ ላይ መድረሱን ገልጸዋል። የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመፍታት በቀጣይ ሁለት ዓመታት ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ አብራርተዋል። በዚህ ዓመትም አስፋልት የማንጠፍ ሥራ እንደሚጀመር ጠቁመዋል።
የጅጋ_ቋሪት_አርብ ገበያ ሎት አንድ የአስፋልት መንገድ በ2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት እየተገነባ ያለ ፕሮጀክት ነው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleወጣቶችን በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።
Next articleየኅብረት ሥራ ማኅበራት ጥራት ያለው ምርትን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ ማኅበረሰብ በማቅረብ ገበያን እያረጋጉ ነው።