ወጣቶችን በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።

3
ደሴ: ጥር 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ሥራ እና ክህሎት መምሪያ ለሥራ ፈላጊዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በትኩረት እየሠራ መኾኑን አስታውቋል።
በቤት እና ቢሮ እቃ ማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩት እነ ደምስ ራህመት እና ጓደኞቻቸው ኅብረት ሥራ ማኅበር ወደ ሥራ ሲገቡ በአነስተኛ ካፒታል መጀመራቸውን እና ከተማ አሥተዳደሩ ብድር እና ቦታ እንዳመቻቸላቸው ተናግረዋል።
የማኅበሩ ሥራ አሥኪያጅ ሰይድ አደም ከተማ አሥተዳደሩ ከግል ድርጅት ጋር በመተባበር ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተገጠመለትን የእንጨት ዲዛይን ማውጫ ማሽን እንደሰጣቸው እና ወደ ሥራ ከገቡ በኋላም ጊዜያቸውን እና ጉልበታቸውን መቆጠብ እንደቻሉ ገልጸዋል።
ማኅበሩ በጥቂት ሰዎች መመሥረቱን አስታውሰዋል። አሁን ላይ ለ16 ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል።
በአምራች የሥራ ዘርፍ የተሰማሩ ወጣቶች የኮምቦልቻ ከተማ የሥራ እና ክህሎት መምሪያ ባመቻቸላቸው የመሥሪያ ቦታ እና ብድር ተጠቅመው ውጤታማ መኾን መጀመራቸውን ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
ከራሳቸው ባሻገርም በየሥራ ዘርፉ ለሌሎች ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻላቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም ጠንክረው በመሥራት ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና ራሳቸውንም ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ሥራ እና ክህሎት መምሪያ ኀላፊ ይትባረክ ጌታሁን በ2018 በጀት ዓመት በከተማዋ ለሚገኙ 20ሺህ ሥራ ፈላጊዎች በአገልግሎት፣ በአምራች እና በኢንዱስትሪ ዘርፎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱንም አንስተዋል።
እስካሁን ለ6ሺህ 720 ሥራ ፈላጊዎች ቋሚ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ያሉት አቶ ይትባረክ ከ2ሺህ በላይ የሚኾኑ ዜጎች ደግሞ በጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲኾኑ መደረጉን አንስተዋል። በኢንዱስትሪ ኢንተርፕራይዝ ምሥረታም በዓመቱ 222 ለመመሥረት ታቅዷል ነው ያሉት።
ኮምቦልቻ ከተማ የኢንዱስትሪ መንደር በመኾኗ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ የምትጫወተው ሚና ላቅ ያለ መኾኑንም ገልጸዋል። በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የመሥሪያ ቦታ እና ብድር ለማመቻቸት መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልኾኑ ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው ብለዋል።
በቀጣይ ወራትም በዕቅዱ መሠረት የተቀመጠውን 20 ሺህ ሥራ ፈላጊዎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲኾኑ መምሪያው በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ሰልሀዲን ሰይድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤቶች የሕዝብ አመኔታ ጠባቂዎች ናቸው።
Next articleየጅጋ_ቋሪት_አርብ ገበያ ሎት አንድ የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክት ምን ላይ ነው?