
ደብረ ታቦር: ጥር 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጥር 25 ቀን በደብረ ታቦር ከተማ የሚከበረውን የቅዱስ መርቆሬዎስ በዓል ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እያከናወኑ መኾኑን የመንበረ ንግሥት ቅድስት ማርያም እና የብስራተ ገብርኤል አሥተዳዳሪ መላከ ፀሐይ መሪጌታ እሸቱ ወርቁ ተናግረዋል፡፡
የቅዱስ መርቆሬዎስን በዓል በልዩ ሁኔታ ለማክበር እና በተክሌ አቋቋም የታጀበ ትዕይንት ለታዳሚው ለማቅረብ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ስለመኾኑም አስረድተዋል፡፡
የደብረ ታቦር ኢየሱስ የተክሌ አቋቋም ጉባኤ ቤት ምስክር መምህር ርዕሰ መምህራን መርሻ መብራቱ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ልዩ እና ብቸኛ በኾነው የተክሌ አቋቋም ሥርዓት የዘንድሮው የቅዱስ መርቆሬዎስ በዓል ደምቆ እንደሚውል ገልጸዋል።
በሀገር በቀል ዕውቀቶች እና ቅርሶች ዙሪያ ሰፊ ጥናት ሲያደርጉ የቆዩት የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ቅርስ አሥተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር እና የአለቃ ገብረሐና የባሕል ጥናት እና ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር መምህር መሠረት ወርቁ በዓሉን በዩኒስኮ ለማስመዝገብ ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑንም ጠቁመዋል።
የደብረ ታቦር ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አሥኪያጅ በኩረ ትጉሃን ሁልጊዜ ዓለማየሁ በበኩላቸው በዓሉን ለማክበር ሊቃውንቱ የዝግጅት ሥራዎችን እያከናወኑ ሲኾን ወጣቶች ደግሞ አድባራትን በማስዋብ ላይ መኾናቸውን ጠቅሰዋል።
“ይህ በዓል ሁሉም አማኝ በጋራ የሚያከብረው እና የሚሳተፍበት ነው” ብለዋል።
ሥራ አሥኪያጁ ለበዓሉ የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል እና ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸው ለጎብኝዎች ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
