ወድቆ መነሳትን በተግባር!

9
ባሕር ዳር: ጥር 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሥራ ዓለም ላይ ከሚያጋጥሙ ችግሮች ውስጥ ኪሳራ አንዱ ነው። በተለይም ደግሞ በንግድ ዓለም ላይ ኪሳራ የማይቀር ነገር ተደርጎም ይወሰዳል።
ኪሳራን እንዴት መቀነስ እና ከኪሳራ እንዴት መነሳት እንደሚገባ ማወቅ እና መዘጋጀት ግን ቀዳሚው ጉዳይ ሊኾን ይገባል።
ውድቆ መነሳትን ካሳዩት ታታሪ ቤተሰብ ውስጥ የቄስ ጌቴው ገብሬ ቤተሰብ ይገኝበታል። ቄስ ጌቴው ገብሬ በንግድ እንቅስቃሴ ላይ ለረጅም ጊዜ አሳልፈዋል። በተሠማሩበት የሥራ መስክ የተሻለ ሃብት ያፈሩ እና የተሻለ ነዋሪም ነበሩ።
ይሁን እንጅ ከዕለታት አንድ ቀን ባጋጠማቸው የንግድ ኪሳራ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ዕዳ ለመክፈል ተገደዱ። የቤት ባለቤት የነበሩት አባውራ ቤት አልባም ኾኑ። በወቅቱ በትምህርት ላይ የነበሩ አራት ልጆቻቸውን እንኳ ለማስተማርም አቅም አጡ።
በወቅቱ ከዋልያ ካፒታል በብድር የተረከቡት የዳቦ መጋገርያ ማሽን ብትተርፍም ሥራ መጀመር የሚያስችል የመሥሪያ ቦታ እንኳ መግኘት አልቻሉም ነበር።
በሂደት ከላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ባገኙት የመሥሪያ ቦታ እና 22 ሺህ ብር ብድር በ2012 ዓ.ም ቤተሰቦቻቸውን ያቀፈ ማኅበር በማቋቋም እና ዳቦ በመጋገር ለማኅበረሰቡ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።
አሁን ላይም በቀን እስከ 500 የተለያዩ የዳቦ አይነቶችን በከተማ አሥተዳደሩ በሚገኙ አምስት የመሸጫ ቦታ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ መኾኑንም ገልጸውልናል።
አካባቢው ወደ ተሟላ ሰላም ተመልሶ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ወደ ሥራ ቢገቡ ደግሞ በቀን አስከ 10 ሺህ ዳቦ ማቅረብ እንደሚቻል ነው ያነሱት።
በኮሌጅ እና በዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ልጆቻቸውን ጭምር ሙያዊ ሥልጠና እንዲያገኙ በማድረግ ወደ ሥራው እንዲገቡ አድርገዋል። አሁን ላይ ለ25 ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻላቸውንም ነው የገለጹት።
ከዳቦ ማቅረብ ባለፈ ሁለት ወፍጮ ቤት በማቋቋም ለከተማው ማኅበረሰብ አገልግሎት እየሠጡ ይገኛሉ።ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ካፒታልም አስመዝግበዋል።
በቀጣይ በትላልቅ ኢንቨስትመንት ላይ ለመሠማራት ማቀዳቸውንም ገልጸዋል። ወጣቶች በተሠማሩበት ሥራ ውጤታማ እንዲኾኑ በመጀመሪያ እራሳቸውን ማሳመን፤ ዕቅድ ማውጣት እና ጽናት ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል።
የሥራ ዕድል የተፈጠረለት ወጣት ሲሳይ ይደርሳል ለሦስት ዓመታት ያህል በማኅበር ተቀጥሮ እየሠራ እንደሚገኝ ነግሮናል። በሚያገኘው ገቢ ራሱን ከመምራት ባለፈ ቤተሰቡን እያገዘ መኾኑን ነው የገለጸው። በራሱ መሥራት የሚያስችል ሙያዊ ልምድ ማግኘቱንም ነው የገለጸው።
ሌላኛዋ የሥራ ዕድል የተፈጠረላት ሀብታም አየነው በማኅበሩ በተፈጠረላቸው የሥራ ዕድል ቤተሰባቸውን ከመምራት ባለፈ ልጆቻቸውን እያስተማሩ መኾኑን አጫውተውናል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article‎”ልጆቼ የእኔ ዕጣ እንዳይደርስባቸው እየታገልኩ ነው” ወጣቷ የልጆች እናት
Next article“ለአማራ መታገል፤ አማራን ማሰቃየት ከኾነ ይቅር” ወደ ሰላም የተመለሰ ወጣት