‎”ልጆቼ የእኔ ዕጣ እንዳይደርስባቸው እየታገልኩ ነው” ወጣቷ የልጆች እናት

15
ባሕር ዳር: ጥር 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎‌የጥር ወር የጋብቻ ወቅት ነው፡፡ ታዲያ በገጠሪቱ የሀገራችን ክፍል የሴት ልጆች ያለዕድሜ ጋብቻ ይፈጸማል፡፡ ‎ባለፉት ሁለት ዓመታትም በአማራ ክልል ባጋጠመው የጸጥታ ችግር ከትምህርት ገበታ ውጭ የኾኑ ሴት ልጆች ላለዕድሜ ጋብቻ ተጋልጠዋል፡፡
‎‌በኢትዮጵያ የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 7 መሠረት ልጆች 18 ዓመት ካልሞላቸው ጋብቻ እንደማይፈጽሙ ይደነግጋል፡፡ ይህም ሴት ልጆችን ለአካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ስለሚዳርግ ነው፡፡
ያለዕድሜ ጋብቻ በሴት ልጆች ላይ የሚያስከትለው ሥነ ልቦናዊ ተጽዕኖስ ምንድን ነው?
‎‌በደቡብ ጎንደር ዞን ነዋሪ የኾነቸው ወጣት ዳሳሽ ቢያዝን በ13 ዓመቷ ወደ ትዳር እንደገባች ትናገራለች፡፡ አሁን ላይ የ20 ዓመት ወጣት ስትኾን ጋብቻው ያለዕድሜዋ ትምህርቷን ከሰባተኛ ክፍል አቋርጣ በወላጆቿ ፍላጎት መፈጸሙን አጫውታናለች፡፡
‎በ16 ዓመቷ የመጀመሪያ ልጇን ባልጠነከረ ሰውነቷ በከፍተኛ የሕክምና ክትትል እንደወለደች ነግራናለች፡፡ ያለዕድሜዋ እናት የኾነችው ወጣት እንደጓደኞቿ ባለመማሯ የበታችነት ስሜት እንደሚሰማትም ገልጻለች፡፡
‎‌በትዳር ውስጥም ብዙ መብቶቿ የተገደበ እንደኾነ ነው ያነሳችልን፡፡ አሁን ላይ የሁለት ልጆች እናት ስትኾን ባለቤቷን በሞት በማጣቷ ልጆቿን ብቻዋን እያሳደገች በከፍተኛ ጫና ውስጥ እንደምትገኝም ተናግራለች፡፡
‎‌ተስፋ ያልቆረጠችው ወጣት በረጅ ድርጅቶች እገዛ በርቀት ትምህርቷን እየተከታተለች 10ኛ ክፍል ደርሳለች። ልጆቸ የእኔ ዕጣ ፈንታ እንዳይደርስባቸው ኑሮየን እየታገልኩ እገኛለሁ ነው ያለችው።
ያለዕድሜ ጋብቻ አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት አድርሶብኛል፤ ጉዳቱን ለመርሳት የሚያስችል ሕክምና እንዳላገኘችም ነግራናለች፡፡
‎‌የወጣቷ ታሪክ ያለዕድሜ ጋብቻ በሴት ልጅ ሕይወት፣ ጤና እና የወደፊት ተስፋ ላይ የሚያደርሰውን ዘርፈ ብዙ ጫና በግልጽ ያሳያል።
‎በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአዕምሮ ሕክምና ስፔሻሊስት የኾኑት ዶክተር ፋኑኤል ጋሻው ያለዕድሜ ጋብቻ ዘርፈ ብዙ ቀውሶች እንደሚያስከትል ተናግረዋል፡፡
‎‌ያለዕድሜ ጋብቻ ልጆች ለአካላዊ እና ጾታዊ ጥቃት ያጋልጣቸዋል። ትምህርታቸውንም አቋርጠው አካላቸው ሳይጠነክር ሲወልዱ ለጤና ችግር እንደሚጋለጡም ተናግረዋል።
‎‌አካሏ እና አእምሮዋ ያልዳበረ ሕጻን ከቤተሰቦቿ እና ከምትኖርበት አካባቢ ተለይታ ወደ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ ስትገባ ሥነ ልቦናዊ ተጽዕኖ እንደሚያመጣም ነው የተናገሩት፡፡
‎‌አብዛኛው ጋብቻ ከፈቃዳቸው ውጭ ስለሚኾን የተስፋ መቁረጥ፣ የአቅመ ቢስነት ስሜት፣ በራስ መተማመን አለመኖር እና ጠንከር ሲልም ከባድ ድብርት፣ ጭንቀት እና ራስን እስከማጥፋት የሚደርስ የእዕምሮ ሕመም እንደሚያስከትል ገልጸዋል፡፡
‎‌አካላቸው ባልጠነከረበት ሁኔታ ልጅ ሲወልዱ ፊስቱላ እና ሌሎች የጤና ችግሮች ይከሰታሉ። ሕጻኑን ለመንከባከብ ስለሚቸገሩ በሕጻኑ ላይ ቀጣይነት ያለው የአዕምሮ ችግር ያመጣልም ብለዋል፡፡
‎‌ያለዕድሜ ጋብቻ መሠረቱ ድህነት ነው ያሉት ስፔሻሊስቱ በዓለም ላይ 12 ሚሊዮን ወጣቶች ያለዕድሜያቸው እንደሚያገቡ ገልጸዋል፡፡ 40 በመቶ የሚኾነው ደግሞ ከሰሃራ በታች ያሉ ድሃ ሀገራት ናቸው ብለዋል፡፡
ችግሩን ለመፍታት ድኅነት ቅነሳ ላይ በሰፊው መሥራት፣ የጸጥታ ችግሩን መቀነስ እና ትምህርትን ማስፋፋት ዋነኛ የመፍትሔ አካል መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡
‎ችግሩ ከተከሰተ በኋላ ሴቶቹን በተለያዩ አማራጮች በማግኘት ሕክምና መስጠት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡ ለዚህም በትምህርት ቤቶች፣ በሚዲያ እና በሃይማኖት ተቋማት በኩል መረጃዎችን ማሠራጨት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ‎‌
ብዙ ጊዜ ባለማወቅ ልጆቹ ላይ የባሕርይ ችግር ሲታይ ልጅ ስለኾነች ነው፤ ከቤተሰብ ስለተለየች ነው በሚል ችላ እንደሚባልም ገልጸዋል፡፡
‎‌በወጣትነታቸው የሚፈጠረው የአዕምሮ ችግር እንዳይቀጥል በቶሎ ሕክምና ካገኙ ችግሮቹ እንደሚፈቱ አስገንዝበዋል፡፡
‎‌እናትን ማከም ልጆችን እና ቤተሰብን ማከም ስለኾነ ሁሉም ባለድርሻ አካል ትብብር ማድረግ እንደሚገባውም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
‎‌ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰላም አማራጭን ባልተቀበሉ ኃይሎች ላይ የተቀናጀ ርምጃ ወሰደ።
Next articleወድቆ መነሳትን በተግባር!