የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰላም አማራጭን ባልተቀበሉ ኃይሎች ላይ የተቀናጀ ርምጃ ወሰደ።

67
ባሕር ዳር፡ ጥር 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎‎በአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰላም አማራጭን ባልተቀበሉ ኃይሎች ላይ በወሰደው የተቀናጀ ርምጃ አንድ የቡድን መሣሪያ (ድሽቃ) መማረኩን ገልጿል።
የሠራዊት አባላቱ በሰሜን ጎጃም በመልኪት (አቅሸት) ቀበሌ ባደረጉት ተከታታይነት ያለው ስምሪት ጽንፈኛ እና ዘራፊ የኾነውን ቡድን እግር በእግር በመከታተል እና ከበባ ውስጥ በማስገባት “ዲ ኬ ኤቲ” የተባለውን ድሽቃ ማርከዋል።
ስምሪቱን የመሩት መቶ አለቃ ገለታ አበበ እንደገለጹት ቡድኑ መሣሪያውን በመጠቀም ማኅበረሰቡን ሲያሸብር መቆየቱን ገልጸዋል።
ጽንፈኛ ቡድኑ ሹፌሮችን፣ ባለሃብቶችን እና ሕፃናትን እያገተ ሰላም ሲነሳ እንደነበርም ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት ግን ቡድኑ ዳግም መነሳት በማይችልበት ደረጃ መመታቱን አረጋግጠዋል።
ስኬቱ የተመዘገበው በቀጣናው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ታኅሣሥ 6/2018 ዓ.ም በአዊ ዞን አዲስ ቅዳም አካባቢ ከሠራዊቱ አባላት ጋር ባደረጉት ውይይት ያስተላለፉትን ትዕዛዝ መሠረት በማድረግ ነው።
ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ በወቅቱ “ጽንፈኛው ከማኅበረሰቡ ዘርፎ የገዛውን ድሽቃ ማርካችሁ ታጠቁት” በማለት የሰጡትን ግዳጅ የቀጣናው የመከላከያ ሠራዊት አባላት በቀን እና በሌሊት በሠሩት ሥራ ውጤት መምጣቱ ነው የተብራራው።
ለዓመታት በታጣቂዎች ዝርፊያ እና ሰላም እጦት ሲሰቃይ የቆየው የአካባቢው ማኅበረሰብ፣ ከሠራዊቱ ጋር በቅንጅት በመሥራቱ ለዚህ ውጤት መብቃቱን መቶ አለቃ ገለታ አበበ ገልጸዋል።
ሠራዊቱ አሁንም በየጫካው የተሸሸጉ የጥፋት ኃይሎችን የማጽዳት ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል መናገራቸውን ከምሥራቅ ዕዝ ሚዲያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለ
Previous article“የደንበኞች ሳምንት ባንኩ ሲሰጥ የቆየውን አገልግሎት የበለጠ ለማቀላጠፍ እና ውጤታማ ሥራ ለመሥራት የሚያስችል ነው” አቶ አህመድ ሽዴ
Next article‎”ልጆቼ የእኔ ዕጣ እንዳይደርስባቸው እየታገልኩ ነው” ወጣቷ የልጆች እናት