
ባሕር ዳር: ጥር 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የግብርና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ አካሂዷል፡፡ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ኀላፊ ፈንታሁን ስጦታው ባለሥልጣኑ የግብርና ምርት እና ምርታማነት ለማሳደግ ጠንካራ ቁጥጥር እያደረገ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ከዘር ብዜት እና አቅርቦት ጋር በተያያዘ የሚባዙ ዘሮችን በማሳ ላይ የቁጥጥር ሥራ ተሠርቷል ብለዋል፡፡ የዘር ብዜቶች ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲኾኑ እንደተሠራም ተናግረዋል፡፡
በዚህ ዓመት 10 ሺህ 783 ሄክታር መሬት በዘር ብዜት ተሸፍኖ 609 ሄክታሩ ደረጃውን ባለማሟላቱ ውድቅ ተደርጓልም ብለዋል፡፡
ወደ ክልሉ የገባውን 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ የፊዚካል ኢንስፔክሽን መሠራቱን ገልጸዋል፡፡
ከችግኝ ጥራት ቁጥጥር አኳያ የፍራፍሬ ልማት ላይ ትኩረት የተሠጣቸው በመኾኑ 542 ሞዴል ችግኝ ጣቢያዎችን በመለየት የዘር ምንጭ ኾነው እንዲያገለግሉ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
የማዳበሪያ ሥርጭት በሥርዓት እንዲመራ መመሪያ ወጥቶ ወደ ሥራ ገብቷል፤ ለዚህም ከአጋር አካላት ጋር የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት፡፡
1 ሺህ 215 ኩንታል ሕገ ወጥ የአፈር ማዳበሪያ ተይዞ ውርስ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡ ተቋሙ እንደክልል ካለው ተግባር ጋር ሲነጻጸር የሰው ኀይል እጥረት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
በባለሥልጣኑ የደብረ ብርሃን ቅርንጫፍ ዳይሬክተር አውግቸው ተሾመ ምርጥ ዘር ከዝግጅቱ ጀምሮ ጥራቱን ጠብቆ ለአርሶ አደሮች እንዲደርስ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ስንዴ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን አንስተው ከደረጃ ውጭ የተሠሩትን በማሳ ላይ እያሉ ውድቅ የተደረጉ መኖራቸውን አንስተዋል፡፡
በባለሥልጣኑ የደሴ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር ብርሃኔ ክብሬ የግብርና ማሳደጊያ ግብዓቶች ቁጥጥር ላይ ከሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
