
ባሕር ዳር: ጥር 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አርሶ አደር ሁሴን ሙሐመድ በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ በንብ ማነብ ሥራ ተሠማርተዋል፡፡ በአካባቢያቸው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ በየዓመቱ እንደሚሠራ ነግረውናል፡፡ ይህም የንብ ማነብ ሥራቸውን ውጤታማ አድርጎታል ብለዋል፡፡
ሥራው ለንቦች ቀሰም፤ ለከብቶቻቸውም መኖ በአግባቡ እንዲያገኙ ማድረጉን ነው የገለጹልን፡፡ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ማር የሚቆርጡ መኾኑን አስታውሰው አሁን ላይ ሁለት እና ሦስት ጊዜ ምርት እንድናገኝ አስችሎናል ብለዋል። 25 የንብ ቀፎዎች እንዳላቸው የነገሩን አርሶ አደር ሁሴን ገቢያቸው ማደጉን እና ኑሯቸው መሻሻሉንም ገልጸዋል።
በአካባቢያቸው ተራቁተው የነበሩ ተራራዎች ወደ አረንጓዴነት እንዲቀየሩ አስችሏል፤ የአፈር መከላትን በመቀነስ የመሬቱን ምርታማነት እንዲጨምር አግዞናል ነው ያሉት። የአካባቢ ጥበቃ ሥራ መጀመሩን አንስተው ኅብረተሰቡ ጥቅሙን ተረድቶ በፈቃደኝነት እየሠራ ነው ብለዋል።
በአማራ ክልል የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የማኅበረ ምጣኔ ሃብት እና ግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያ እንዲሁም ተመራማሪ ያልፋል ተመስገን (ዶ.ር) የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ ሥነ ምህዳሩን መጠበቅ ዋነኛ ተግባሩ እንደኾነ ለአሚኮ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም የግብርና ምርት እና ምርታማነትን ለመጨመር ያግዛል። ይህም የአርሶ አደሮችን ገቢ ከፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ እንደ ክልል በተደረጉ ጥናቶች የስንዴ ምርት ላይ እስከ 20 በመቶ እና የጤፍ ምርትን እስከ 50 በመቶ የምርት ጭማሪ እንዲኖር ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡
ሥራው ለረጅም ጊዜ በተከታታይ ከተሠራ የአፈር ተፈጥሯዊ ንጥረ ነገርን በመጨመር ለሰው ሠራሽ ማዳበሪያ የሚወጣውን ወጭ እንደሚቀንስም አስረድተዋል፡፡
የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራዎች የተቦረቦሩ መሬቶችን ወደ ልማት በመመለስ ተጨማሪ የሚታረሱ መሬቶች እንዲኖሩ ያደርጋል። ይህም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡ በክልሉ ሙሉ በሙሉ አፈር ጠርጎ ይዞት ይሄድ የነበረውን የውኃ ፍስሰት 38 በመቶ መቀነሱንም ተናግረዋል፡፡
የተለያዩ የገቢ አማራጮች ወይም የሥራ ዕድል ለመፍጠር አስችሏልም ነው ያሉት፡፡ የአካባቢው ሥነ ምህዳር ሲመለስ ንብ ለማነብ እና ለከብቶች መኖ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል። ከብት በማድለብ፣ በደን ልማት፣ በአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት እና የእንስሳት መኖን በማልማት በተለይም ወጣቶች ተጠቃሚ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡
የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ በመኾኑ በተደራጀ መንገድ ስለመሠራቱም አንስተዋል፡፡ ሥራው ቀጣይነት እንዲኖረው አርሶ አደሮች ከልማቱ ተጠቃሚ መኾን አለባቸው፡፡ ለአብነትም ለከብቶቻቸው ዓመቱን ሙሉ መኖ ማግኘት እንዲችሉ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡
ይህም ጥቅሙን ተረድተው በራሳቸው ተነሳሽነት እና በባለቤትነት እንዲይዙት እና ዘላቂነት እንዲኖረው ያስችላል ብለዋል፡፡
የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራው ተጠቃሚነቱን ከፍ ለማድረግ የየአካባቢውን ሥነ ምኅዳር ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎችን መሥራት ያስፈልጋል ሲሉም መክረዋል። የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ጊዜውን መሠረት ያደረገ ሊኾን እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
