
ባሕርዳር፡ ጥር 18/2018ዓ.ም (አሚኮ) የአስፋልት መንገዶች ለአንድ ሀገር የተቀላጠፈ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ያላቸው ፋይዳ ጉልህ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ደግሞ ይህን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው መሠረተ ልማት ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ትገኛለች።
ከሚሠሩ የመንገድ መሠረተ ልማቶች መካከል በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን እየተሠራ የሚገኘው የደምበጫ- ፈረስቤት- ቢቡኝ ሎት አንድ አስፋልት መንገድ ፕሮጀክት አንዱ ነው። ይህ 69 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር መንገድ በ2013 ዓ.ም ነበር በአንድ ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በጀት ግንባታው የጀመረው።
የመንገድ ፕሮጀክቱን በቀደመ መጠሪያው የአማራ መንገድ ሥራዎች የአሁኑ ኅብር ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጭ ነው እየሠራ የሚገኘው።
መንገዱ በሦሥት ዓመት ተሠርቶ ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረ ቢኾንም ከአራት ዓመት በላይ ኾኖትም አልተጠናቀቀም። ይህን ተከትሎም የአካባቢው ነዋሪዎች የአስፋልት መንገዱ በአጭር ጊዜ ተሠርቶ እንዲጠናቀቅ ጠይቀዋል።
መንገዱ የማኅበረሰቡ የረጅም ዓመታት ጥያቄ የነበረ ቢኾንም በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ግን የሚጠናቀቅበት ጊዜ ተራዝሟል ሲሉም አክለዋል።
መንገዱ የሚያልፍባቸው አካባዎች ላይ የሚገኙ የልማት ተነሺዎች ለልማቱ ባላቸው ፍላጎት የዘሩትን እህል በተገቢ ሁኔታ ሳይሸከፍ እና ለፈረሰባቸው ቤት ካሳ ሳይቀበሉ እንደቀሩም አንስተዋል።
የልማት ተነሺዎች የካሳ ጉዳይም እስከ አሁን መፍትሄ አላገኘም ነው ያሉት። የመንገድ ሥራውን የመከታተል እና የመቆጣጠር ውስንነት አለ፤ ሕዝቡ መልማት ይፈልጋል፤ የመንገድ ግንባታውም ሊቀጥልልን ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል።
የመንገድ ፕሮጀክቱ አማካሪ የጄ ኤንድ ኬ ፕሮጀክቶች ሳይት መሐንዲስ ኢንጂነር ፈለቀ አምዴ በነዋሪዎች የተነሱ ጥያቄዎች ተገቢነት ያላቸው መኾኑን ተናግረዋል።
በአካባቢው ያለ የጸጥታ ኹኔታ ግን የግንባታ ማሽነሪ እና ተሽከርካሪዎችን ወደ ፕሮጀክቱ ለማስገባት አስቸጋሪ በማድረጉ የመንገድ ፕሮጀክቱን እንዳጓተተው አንስተዋል።
በአካባቢው እና በክልሉ ያሉ መንግሥታዊ ያልኾኑ የግንባታ መሳሪያ ባለቤቶች እና መንግሥታዊ ድርጅቶች ማሽነሪ እና ተሽከርካሪ ለማከራየት ፈቃደኛ አለመኾናቸውም ሌላኛው ችግር መኾኑን ተናግረዋል። የካሳ ክፍያ፣ በከተሞች ያለው የመብራት እና የውኃ መስመር አለመነሳት፣ የተጠየቁ የአፈር እና የድንጋይ ማምረቻ ቦታዎች ለኮንትራክተሩ በቶሎ አለመለቀቅ፣ የግንባታ እቃዎች ዋጋ ጭማሪ በመንገድ ፕሮጀክቱ የተስተዋሉ ሌሎች ችግሮች ናቸው ብለዋል።
አሁን ላይ የአስፋልት ማንጠፍ ፣ የውኃ መውረጃ ቦይ ግንባታ ፣ የውኃ ቱቦ ቀበራ እና ተያያዥ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።
የፕሮጀክቱን አፈጻጸም ለማሻሻል ከዚህ በፊት ከነበረው የተሻለ የዞን እና የክልል ሥራ ኀላፊዎች ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የቡሬ አካባቢ ፕሮጀክቶች ማኔጀመንት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኢንጅነር ሁሉ አለምነህ ደግሞ አብዛኛዎቹ ያጋጠሙ ችግሮች ከጸጥታ ችግሩ ጋር የሚገናኙ ቢኾንም የጸጥታ ችግሩ ከመፈጠሩ በፊት የኮንትራክተሩ አቅም ላይ ውስንነት ታይቶ እንደነበር ተናግረዋል።
በ2015 ዓ.ም የጸጥታ ችግሩ ከመፈጠሩ በፊት የአመራር ለውጥ እና ተያያዥ ሥራዎች በመሠራታቸው የአስፋልት ንጣፍን ጨምሮ ሌሎች የተሻሉ ሥራዎች መሥራት መቻሉን አስታውሰዋል። ከ2015 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ደግሞ ሙሉ በሙሉ የመንገድ ፕሮጀክቱ ሥራ ቁሞ እንደነበር ተናግረዋል።
አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩም አሁን ላይ ሁሉንም ዓይነት ሥራዎች (የአስፋልት፣ የቆረጣ፣ የማፋሰሻ ቦዮች ሥራ እና መሰል ሥራዎች) እየተሠሩ መኾኑን ጠቅሰዋል። በሚፈለገው ልክ ግን አይደለም ነው ያሉት።
የመንገድ ፕሮጀክቱም አሁን ላይ 31 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል። በቀጣይ ሁለት ዓመት ውስጥ ደግሞ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ከማሺነሪ እና ተሽከርካሪ ኪራይ ጋር ተያይዞ ተቋራጩ ለገጠመው ችግር መፍትሄ ለማምጣት በአካባቢው ያሉ የማሺነሪ አከራይ ባለሃብቶች እና የዞን አሥተዳደሩን ጨምሮ የሚመለታቸው የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት ውይይት መደረጉን አንስተዋል።
ከልማት ተነሺዎች ካሳ ክፍያ ጋር ተያይዞም በቀደመው አዋጅ በኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የፋይናንስ ክፍል ተሠርቶ ወረፋ የሚጠብቁ የገጠር መሬትን እና ተያያዥ የካሳ ክፍያዎች እየታዩ ይከፈላሉ ነው ያሉት።
የከተማ ቦታዎች የካሳ ክፍያዎች በተመለከተ ደግሞ ተሠርተው ተጠናቅቀው ወደ ኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የደረሱት አዲሱ አዋጅ ከወጣ በኋላ በመኾኑ እና አዋጁ ጉዳዩን ለክልሎች የሰጠ በመኾኑ የእነሱ ጉዳይ በክልሉ መንግሥት በኩል መፍትሔ ያገኛል ነው ያሉት።
በዚህ ዓመትም የአስፋልት ንጣፍ ተጀምሯል ያሉት ኢንጅነር ሁሉ የጸጥታ ሁኔታው ግን አሁንም በሚፈለገው ልክ ፕሮጀክቱን ለማስኬድ አስቸጋሪ ስለኾነ በየደረጃው የሚገኙ የሥራ ኀላፊዎች እገዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
