
ባሕር ዳር፡ ጥር 18/2018ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የግብርና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አጀበ ስንሻው የክልሉን የአሻጋሪ እና ዘላቂ ልማት ዕቅድ ለማሳካት የግብርናውን ዘርፍ በቴክኖሎጂ ማገዝ ያስፈልጋል ብለዋል። ይህም የምርጥ ዘር፣ የማዳበሪያ፣ የኬሚካል እና ሌሎች ቴክኖሎጅዎችን እንደሚያካትት ተናግረዋል።
የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ጤናማ እና ውጤታማ ለማድረግ የግብርና ጥራት እና ደኅንነት ባለሥልጣን የማይተካ ሚና አለው ነው ያሉት። ተቋሙን ማጠናከር የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚውን ዕድገት የበለጠ እንደሚያጠናክርም ገልጸዋል።
ምርትን ለማሳደግ የምርጥ ዘር እና ማዳበሪያ አቅርቦት እና አጠቃቀም ከፍተኛውን ድርሻ ስለሚይዝ ጥራቱን የጠበቀ መኾን እንዳለበትም አንስተዋል።
ተቋሙ ኬሚካሎች ጥራታቸውን ጠብቀው በአግባቡ እንዲቀርቡ እና ጥቅም ላይ እንዲውሉ ትልቅ ኀላፊነት አለበት ነው ያሉት።
በቀጣይም ለሰው ሕይዎት ተስማሚ እና ለገበያ የሚቀርበው ምርት ጥራቱን የጠበቀ እንዲኾን እንደሚሠራ አመላክተዋል። የተቋሙ መጠናከር ግብርናውን ማጎልበት ነው፤ ይህ ደግሞ ኢኮኖሚውን ያጎለብታል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወንዳለ ሀብታሙ (ዶ.ር) የግብርና ግብዓቶች ቁጥጥር ካልተደረገባቸው ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ ከፍተኛ ውድመት ሊያስከትሉ ይችላሉ ብለዋል። የኬሚካል ቁጥጥር ሥራው ዓለም አቀፍ ሕጉን ተከትሎ መኾን እንዳለበትም ተናግረዋል።
ዘር በጥንቃቄ መጓጓዝ ያለበት ውድ ሃብት ነው ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ችግር ይዞ ሊመጣ ስለሚችል የቁጥጥር ሥራው መጠናከር እንዳለበት ገልጸዋል። ለአብነትም በማንጎ ምርት የተፈጠረውን ችግር አንስተዋል።
የማዳበሪያ ቁጥጥርም በተገቢው መንገድ መኾን እንዳለበት አሳስበዋል። ቁጥጥሩም ከመጠን ባለፈ በውስጡ ያለውን ንጥረ ነገር መሠረት ያደረገ ሊኾን ይገባል ነው ያሉት።
የቁጥጥር ሥራው መጠናከር በሰዎች፣ በእንስሳት፣ በአካባቢ ላይ የሚደርስን ጉዳት በመከላከል ዘላቂ ልማት ለማምጣት ጉልህ ሚና እንዳለው አስገንዝበዋል። ለዚህም የሚመለከታቸው አካላት በትብብር መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፦ ፍሬሕይዎት አዘዘው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለ
