
እንጅባራ: ጥር 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአዊ ብሔረሰብ ምክር ቤት 4ኛ ዙር 34ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።
የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ሙሉዓዳም እጅጉ ባለፉት ስድስት ወራት በሰላም እጦት ምክንያት በትምህርት ዘርፉ ያጋጠሙ ስብራቶችን ለመጠገን የተወሰዱ እርምጃዎች አበረታች መኾናቸውን ገልጸዋል።
ዘርፉ ሙሉ በሙሉ ከችግሩ እንዲወጣ በየደረጃው ያሉ የምክር ቤት አባላት ተግባሩን በትኩረት በመያዝ መፈጸም እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በሁሉም ዘርፍ የተመዘገቡ በርካታ ስኬቶች የመኖራቸውን ያህል ዛሬም የመሪዎችን ቁርጠኝነት የሚሹ ተግባራት መኖራቸውን ተናግረዋል።
የግብርና ሥራን ለማዘመን የተጀመሩ ሥራዎችን ማስፋት፤ ሥራ አጥነትን መቀነስ እና የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መኾናቸውንም አንስተዋል።
በተቋማት የሚሰጠው አገልግሎት ወቅቱን የሚመጥን፤ የዜጎችን እንግልት የሚቀንስ፤ ጊዜን፣ ጉልበትን እና ገንዘብን ቆጣቢ መኾን ይገባልም ነው ያሉት። እያደገ የመጣውን የልማት ፍላጎት ለመመለስ የገቢ አሰባሰብ አቅም ማሳደግ እንደሚገባም አንስተዋል።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ እየታየ ያለውን አንጻራዊ ሰላም ለማጽናት ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ወገኖች የሰላም አማራጭ እንዲከተሉ ግፊት ማድረግ ያስፈልጋልም ብለዋል።
ምክር ቤቱ በአንድ ቀን ውሎው የባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ እና የከፍተኛ ፍርድ ቤት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርትን ገምግሞ በማጽደቅ እና የተጓደሉ የአሥፈጻሚ ተቋማትን ሹመት በማጽደቅ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ዘጋቢ:- ሳሙኤል አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
