ዘላቂው መፍትሔ ሰላም መስፈኑ ነው፡፡

19
ባሕር ዳር: ጥር 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ወጣት እውነቱ ጌትነት በደቡብ ጎንደር ዞን የወገዳ ከተማ አሥተዳደር ነዋሪ ነው፡፡ አካል ጉዳተኛ በመኾኑ እንደልቡ ተንቀሳቅሶ መሥራት አይችልም፡፡ አልተማረም፤ ረዳት ዘመድም የለውም፡፡
ይኹን እንጂ ለመኖር አቅሙ የፈቀደለትን ሁሉ በመሥራት ይተዳደራል፡፡ ሊስትሮ እና ሱቅ በደረቴ የኑሮው መሰረት አድርጎ ባለበት ሁኔታ በክልሉ የተከሰተው ግጭት ሌላ ፈተና ፈጠረበት፡፡
ግጭቱ እና የኑሮ ውድነት ከአካል ጉዳተኝነቱ ጋር ተጋግዘው የሕይወት ፈተናን አከበዱበት፡፡
በልቶ ለማደር መሥራት ፈተና ቢኾንበትም ድንገት ግጭት ተከስቶ ተኩስ ሲከፈት እንደሌሎቹ ፈጥኖ ራሱን ከችግር ለማሸሽ አለመቻሉ ስቃዩን አበዛበት፤ አደጋውን አቀረበበት፡፡
ግጭት እና ወንጀል ሲበዛም “መረጃ አቀባይነህ” እየተባለ በታጣቂዎች መጠርጠርም አጋጠመው፡፡ የማይችል አካሉም ተደበደበ፡፡
እውነቱ ከመሞት መሰንበት ብሎ በ2016 ዓ.ም አካባቢውን ለቅቆ ተሰደደ፡፡ ባሕር ዳርን መዳረሻው አደረገ፡፡
ባሕር ዳር ከተማ ቢያንስ ሰላም ስለኾነች የጥይት ተኩስ አይረብሸውም፤ ሮጦ ማምለጥ ግድ አይኾንበትም፡፡ ለእሱ ሰላም ካለ ሌላው ቀላል ነው፡፡
አሁን ላይ በዌልቼር እየተንቀሳቀሰ ሚዛን ይሠራል፤ ችግሩ ሲጠናበት ግን የሰዎችን እጅም ያያል፡፡
እዚህ ላይም የደንብ አስከባሪ ክልከላ አለ፡፡ እንዲሠራበት የተፈቀደለት ቦታ ደግሞ ሰዎች ስለማይበዙበት ተመዛኝ አያገኝም፡፡ ኹኔታዎች ከተመቻቹለት በመነጽር ሽያጭ ለመተዳደር እቅድ አለው፡፡
አካል ጉዳተኝነቱ ሳያግደው ሠርቶ ለማደር ትልቅ ጉጉት እና ጅምር ቢኖረውም የሰላም እጦቱ ችግር እንደኾነበት ይናገራል፡፡
ግጭት እንኳን እንደልቡ ለማይንቀሳቀስ አካል ጉዳተኛ ለጤነኛው ሰውም አስቸጋሪ ነው፡፡
በሀሳብ፣ በገንዘብም ኾነ በሌሎች መንገዶች የሚያግዘው ካገኘ ከልመና ይልቅ ሠርቶ ለማደር ከፍተኛ ጉጉት አለው፡፡ አስተማማኝ ሰላም ሳይኖር ወደ ቀየው ለመመለስ እንደሚቸገር የገለጸው እውነቱ ሰላም እንዲፈጠር ይመኛል፡፡
የሰላም እጦቱ እንደ እውነቱ ዓይነት በርካታ አካል ጉዳተኞችን ስቃይ አብዝቷል፡፡
ኅብረተሰቡም ኾነ መንግሥት ጊዜያዊ ድጋፍ ማድረጋቸው መልካም ነው፡፡ ለዘላቂው መፍትሄ ግን ሰላም መስፈኑን ነው እውነቱ የሚመኘው፡፡
ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየግልግል ዳኝነት በማንኛውም የንግድ እና ኢንቨስትመንት ውሎች ላይ የሚካተት የአሠራር ሥርዓት ነው።
Next articleከ2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 79 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጠ።