
ባሕር ዳር: ጥር 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር “የሕግ የበላይነት እና አማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴዎች ለዘላቂ ሰላም እና ልማት” በሚል መሪ መልዕክት ኮንፈረንስ አካሂዷል።
በኮንፈረንሱ እየተሳተፉ ያገኘናቸው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኾልዲንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ (ዶ.ር) የግልግል ዳኝነት በማንኛውም የንግድ እና ኢንቨስትመንት ውሎች ላይ የሚካተት የአሠራር ሥርዓት መኾኑን ተናግረዋል።
በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ግልጽ የኾነ የሕግ እና አሠራር ሥርዓት ወሳኝነት ያለው መኾኑን ጠቁመዋል። ባለሃብቶች በተለያዩ ሀገራት ኢንቨስት ሲያደርጉ በየሀገራት ውስጥ ያለውን የውስጥ አሠራር እንዳለ ኾኖ የግልግል ዳኝነት አሠራሮችንም ከግምት ውስጥ እንደሚያስገቡ ይናገራሉ።
ከኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘ በሚፈጠሩ አለመግባባቶች ወደ ፍርድ ቤት ሲሄዱ ፍትሐዊ ፍርድ አላገኝም የሚል ስጋትን የሚፈጥር ስለኾነ የግልግል ዳኝነት ሥርዓት ይህንን ስጋት የሚፈታ ነው ብለዋል።
በእንደዚህ አይነት ውይይትም የጋራ አድርጎ ተግባራዊ ማድረግ ወሳኝ ስለመኾኑ አንስተዋል።
ዓለም ዓቀፋዊ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ ገለልተኝነትን ያማከለ የዳኝነት ሥርዓት መሥጠት እንደሚጠይቅ አንስተዋል። ለዚህም በኢትዮጵያ የግልግል ዳኝነት ማዕከል ለመገንባት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሥራውን መጀመሩ የሚበረታታ መኾኑን አንስተዋል።
ኮንፈረንሱ በባሕር ዳር እስከ አሁን የተሠሩ ሥራዎችን ለሌሎች አካላት ግንዛቤ በመፍጠር፣ ከተማዋን ለማስተዋወቅ፣ ባለሙያዎችን ለማብቃት፣ በከተማዋ የግልግል ዳኝነት ማዕከሉን ለማቋቋም የሚያስፈልጉ ቅድመ ዝግጅቶችን እና አቅሞችን ለሚመለከታቸው አካላት እንዲያውቁት የሚያደርግ ስለመኾኑም ተናግረዋል።
ከተማዋ እያከናወነችው ያለውን የልማት ሥራዎችን እና የምቹ የቱሪዝም መዳረሻነቷንም አጉልቶ ለማሳየት ሚናው የጎላ ስለመኾኑም አመላክተዋል።
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይህንን ኮንፈረንስ ማዘጋጀታቸው የሚበረታታ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
