
ባሕር ዳር: ጥር 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር “የሕግ የበላይነት እና አማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴዎች ለዘላቂ ሰላም እና ልማት” በሚል መሪ መልዕክት ያዘጋጀው ኮንፈረንስ እንደቀጠለ ነው።
በዛሬው መርሐ ግብር የተለያዩ ሀሳቦች እየቀረቡም ውይይት እየተደረገባቸው ይገኛል።ግልግል ዳኝነት ለዘላቂ ኢኮኖሚ እድገት በሚኖረው ሚና በተመለከተ መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት በፍትሕ ሚኒስቴር የፍትሐብሔር ጉዳዮች ምክትል ዋና ዳይሬክተር ንጉሤ ትዛዙ የግልግል ዳኝነት ገለልተኛ የኾነ ፍርድ የሚሰጥበት በመኾኑ ለዘላቂ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ እንዳላቸው ገልጸዋል።በመደበኛ ፍርድ ቤቶች የማናገኛቸውን የዳኝነት አማራጮችን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያስችሉም ተናግረዋል። የግልግል ዳኝነት ከኢንቨስትመንት አንጻር የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን የሚፈቱ በመኾናቸው ለኢንቨስትመንት መስፋፋትም ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል።
ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች ባለፈ በቢዝነስ ዘርፉ ዕውቀት ባላቸው አሸማጋዮች የሚፈጸም የግጭት መፍቻ መንገዶች በመኾናቸውም የግልግል ዳኝነት ጠቀሜታ ያላቸው መኾናቸውን ገልጸዋል። ካላቸው ባህሪ አንጻርም ውስብስብ ለኾኑ እና ለኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች አማራጭ የግጭት መፍቻ ኾነው ያገለግላሉ ብለዋል። አንዱ የልማት ዘርፍ በመኾንም ለዘላቂ ልማት ዘርፍ አጋዥ መኾኑን ጠቁመዋል። “የግልግል ዳኝነት ኢንቨስትመንትን በማበረታታትም ለዘላቂ ኢኮኖሚ እድገት ሚናው የጎላ ስለመኾኑም” አንስተዋል። በኢትዮጵያም በግልግል ዳኝነት የቆዩ ልምዶች ስለመኖራቸው አንስተዋል። በየስምምነቶችም የግልግል ዳኝነቶችን እውቅና ሰጥታ ቀደም ብላ የጀመረችበት እና ሥትሠራበት የቆየች መኾኗን አንስተዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
