“የተሃድሶ ሠልጣኞች ሰላምን በመምረጣችሁ ልትመሰገኑ ይገባል” አቶ በሪሁን መንግሥቱ

15
ጎንደር: ጥር 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ለሦስተኛ ዙር የቀድሞ ታጣቂዎች ምርቃት እና የሽኝት መርሐ ግብርን በጎንደር ከተማ በጠዳ ማዕከል አካሂዷል።
በዕለቱ የተገኙት የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ በሪሁን መንግሥቱ በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በሰብዓዊ፣ በኢኮኖሚ እና በማኅበራዊ ዘርፍ ጉዳት ማድረሱን አንስተዋል። በዚህም በሕዝቡ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ላይ ጫና አሳድሮ ቆይቷል ነው ያሉት። “የተሃድሶ ሠልጣኞች ሰላምን በመምረጣች ልትመሰገኑ ይገባል” ብለዋል።
ለብሔራዊ ጥቅም እና ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የሰላምን አማራጭ መከተል አትራፊው መንገድ እንደኾነም አስረድተዋል።
ከግጭት አዙሪት መውጫ መንገዱ ሰላም እና ልማት በመኾኑ በቀጣይ ሰላምን በማጽናት በልማት እንቅስቃሴ ሊሳተፉ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በቀጣይ የቀድሞ ታጣቂ ኃይሎችን በሥራ ዕድል ፈጠራ እና በተለያዩ ዘርፎች መልሶ ማቋቋም ላይ በትኩረት እንደሚሠራ ምክትል ኀላፊው ተናግረዋል።
ፉክክር እና ግድያን በማራቅ የሰላምን አማራጭ በመቀበል የክልሉን ሕዝብ መካስ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል። በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭ እንዲቀበሉ በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የዲሞብላይዜሽን ዳይሬክተር እና የጠዳ ማዕከል አሥተባባሪ ኮሎኔል ጎሳዬ ጥላሁን የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን በአማራ ክልል የተደረገውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የሰላም ጥሪን የተቀበሉ ከ13 ሺህ በላይ ለሚኾኑ የቀድሞ ታጣቂዎች ሥልጠና በመስጠት ወደ ማኅበረሰቡ እየቀላቀለ እንደሚገኝ አንስተዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራር የኾኑት ብርጋዴል ጀኔራል መካሻ ጀንበሬ የሀገርን አንድነት፣ ልማት እና ሰላምን ለማጽናት አብሮ መቆም ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) ወታደራዊ አሥተዳደር መምሪያ ኀላፊ ረዳት ፕሮፌሰር እያሱ አባተ በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር እርስ በእርስ እንድንገዳደል አድርጎናል ብለዋል። ትግሉ የአማራ ሕዝብን ዘላቂ ሰላም የሚያሳጣ እና የሀገርን አንድነት የሚያፈርስ በመኾኑ ወደዘላቂ ሰላም ስምምነት መምጣታቸውን አስረድተዋል።
ስምምነት መፈጸሙ ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ በር የከፈተ መኾኑንም አንስተዋል።
ሌሎች የተሃድሶ ሠልጣኞችም በቀጣይ ሰላምን ለማጽናት የበኩላቸውን እንደሚወጡ መልእክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article86ኛው የአገው ፈረሰኞች ባሕል በአዲስ አበባ ከተማ ተከበረ።
Next articleየግልግል ዳኝነት ኢንቨስትመንትን በማበረታታት ለዘላቂ ኢኮኖሚ እድገት ሚናው የጎላ ነው።