
አዲስ አበባ: ጥር 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከታላቁ ዓድዋ ድል ማግሥት ጀምሮ የተመሠረተው የአገው ፈረሰኞች ባሕል 86 ዓመታትን አስቆጥሯል።
በታላቁ ዓድዋ ድል የአገው ሕዝብ እና ፈረሶቹ ያበረከቱትን ታላቅ አስተዋጽኦ ለመዘከር በሚል የተመሠረተው እና ከ62 ሺህ በላይ አባላት ያሉት የአገው ፈረሰኞች ማኅበር በ2018 ዓ.ም 86ኛ ዓመት ክብረ በዓሉ በአዲስ አበባ ተከብሯል።
ባሕሉ በተለይ በአማራ ክልል በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር በየዓመቱ ጥር 23 በታላቅ ድምቀት የሚከበር ሲኾን በአዲስ አበባ የሚገኙ የአገው ተወላጆች ደግሞ ለ3ኛ ጊዜ የ2018 ዓ.ም 86ኛውን በዓል በቦሌ ክፍለ ከተማ አዳራሽ በተለያዩ ዝግጅቶች አክብረዋል።
የአገው ሕዝብ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ከተፈጥሮ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ነው ያሉት የኮሚቴው የአዲስ አበባ ሰብሳቢ ስለሺ አስፋው ናቸው።
የአገው አርበኞች በዓድዋ ድል ያበረከቱት አስተዋፅኦ ታሪክ የሚዘክረው ነው ብለዋል። የአሁኑ ትውልድ ይህንን የአገው ሕዝብ ታሪክ እና ጀግንነት እየዘከረ የሚገኘው የፈረሱን እና የአርበኛውን ትስስር ለማውሳት እንደኾነ ገልጸዋል።
የዕለቱ የክብር እንግዳ ጸሐፊ ተውኔት አያልነህ ሙላት ባደረጉት ንግግር የአገው ማኅበረሰብ ፈረስን አዳቅሎ ለዓለም ያስተዋወቀ መኾኑን ተናግረዋል።
የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ጠንካራ የኾነ ትልቅ ማኅበር ነውም ብለዋል። ይህ ማኅበር እና ባሕሉ የሕዝቡን ዕሴት፣ ማንነት እና ባሕል በተናበበ እና በተጠናከረ ሁኔታ ኢትዮጵያዊ አንድነትን በተላበሰ መልኩ ዋናውን ማኅበር ሳይጋፋ መከበር እና መተዋወቅም እንደሚገባው አሳስበዋል።
በዕለቱ ሙዚቃዎች፣ ሥነ ጽሑፎች፣ የቁንጅና ውድድር፣ የባሕል ምግቦች እና ሌሎች ዝግጅቶች ቀርበዋል።
ዘጋቢ:- ድልነሳ መንግሥቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
