ለአፍሪካውያን ጥሩ እይታ ያላቸው ፕሬዝዳንት

21
ባሕር ዳር፡ ጥር 17/2018ዓ.ም (አሚኮ) በዚህ ሳምንት ጥር 12/1953 ዓ.ም የኢትዮጵያ ባለውለታ ጆን ፊዝጄራልድ ኬኔዲ (ጆን ኤፍ ኬኔዲ) 35ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ኾነው ቃለ የፈጸሙበት ጊዜ ነበር።
ይህ ሰው በኢትዮጵያ ብዙ የሚታወሱባቸው ነገሮች አሏቸው። ከእነዚህም መካከል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ኬነዲ ቤተ መጻሕፍት የሚጠቀስ ሲኾን ፕሬዝዳንቱ እንዳስገነቡት ይነገራል። ይህ ቤተ መጻሕፍት ሁሌም የሚታወሱበት ነው፡፡
ኬኔዲ በሥልጣን በቆዩበት አጭር ጊዜ ውስጥ ቁጥራቸው ከ20 በላይ ነጻ የአፍሪካ ሀገር መሪዎችን ወይም አምባሳደሮቻቸውን በኋይት ሐውስ ተቀብለው አነጋግረዋል። ፕሬዝዳንቱ ኢትዮጵያን በልዩ ሁኔታ እንደሚረዱም ነው የሚገለጸው።
ምንጭ በሮበርት ዳሌክ የተጻፈ አን አንፊኒሽድ ላይፍ ጆን ኤፍ ኬነዲ የተሰኘ መጽሐፍ።
👉 የንጉሱ ከስደት ወደ ሀገር መመለስ
ጥር 12/1933 ዓ.ም በዚህ ሳምንት ከዛሬ 85 ዓመት በፊት ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ መሬት ገብተው ኦሜድላ ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ የሰቀሉበት ዕለት ነበር፡፡
ኢትዮጵያ በጣሊያን ወራሪ ኃይል በተወረረች ጊዜ ንጉሡ ኃይለ ሥላሴ የኢትዮጵያን ጉዳይ በጄኔቫ ለሊግ ኦፍ ኔሽን እንዲያቀርቡ ስምምነት ላይ ተደርሶ ወደዛው አቀኑ፡፡
ንጉሱ በአውሮፓ በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ሲመክሩ እና ለሀገራቸው ፍትሕ እንዲሰጥ ሲከራከሩ ጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን አርበኞች ደግሞ ለሀገራቸው ሰንደቅ ይዋደቁ ነበር፡፡
በመጨረሻም ጣሊያን የጀግኖቹን ትግል እና ቆራጥነት መቋቋም ሲያቅተው ኢትዮጵያን ለቆ ለመውጣት ተገደደ፡፡ ይህኔ ታዲያ ኢትዮጵያውያን ንጉሣቸውን ይቀበሉ ዘንድ ተዘጋጁ፡፡ ንጉሡም ለሀገራቸው ሲሠሩ የቆዩት የዲፕሎማሲ ሥራ ፍሬ በማፍራቱ እና ሀገራቸው ነጻ በመውጣቷ ወደ ሀገራቸው ተመለሱ፡፡ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማም ከፍ አድርገው ሰቀሉ።
ምንጭ፦ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የተጻፈ ሕይወቱ እና የኢትዮጵያ እርምጃ መጽሐፍ።
👉 ብቸኛው ዋንጫ
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን በመመሥረት ትልቅ ባለውለታ ናት። ከመመሥረት በተጨማሪም በመጀመሪያዎቹ ውድድሮች በመሳተፍ እና ውድድሩን በማዘጋጀትም ጭምር የእግር ኳስ ሀገር ናት።
ሦስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ማሸነፏ ደግሞ በመሠረተችው ውድድር የምትናገረው ታሪክ እንዲኖራት አድርጓል። ጊዜው 1954 ዓ.ም ነው። ሦስተኛው የአፋሪካ ዋንጫ በአዲስ አበባ በያኔው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስታድየም ሲካሄድ ኢትዮጵያ አዘጋጅ ነበረች፡፡
በመጨረሻም ኢትዮጵያ ከግብጽ ያደረጉት ጨዋታ በኢትዮጵያ 4ለ2 አሸናፊነት ተጠናቀቀ። በአፍሪካ ዋንጫም የኢትዮጵያ ብቸኛው የዋንጫ ድልም ይህ ኾነ። ይህ ድል ከተገኘ በዚህ ሳምንት 64 ዓመት ሞላው።
ምንጭ፦ በገነነ መኩሪያ የተጻፈው ሊብሮ መጽሐፍ።
በምስጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለ
Previous articleየተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በደቡብ ጎንደር ዞን በርካታ ታጣቂዎች ገቡ።
Next article“ለኢትዮጵያ አየር ኃይል ሰማይ ወሰን ኾኖ አያውቅም” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ