
ደብረ ታቦር: ጥር 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል መንግሥት እና በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በደቡብ ጎንደር ዞን ታች ጋይንት፣ ላይ ጋይንት እና አጎራባች ወረዳዎች ነፍጥ አንግበው በጫካ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች ከነሙሉ ትጥቃቸው ወደ ሰላም ገብተዋል።
አዲሱ ደባልቄ የገብረየ ክፍለ ጦር አዛዥ፤
መላኩ ዋለልኝ የአንበሳው ጋይንት ክፍለ ጦር አዛዥ፤ ባንቲቁም አበባው የራስ ጉና ክፍለ ጦር አዛዥ እና አባሎቻቸው ናቸው ወደ ሰላም የገቡት።
የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ ትናንትን ረስቶ ነገን በማሰብ እና የሕዝብን ችግር በመረዳት የሰላም ምርጫን መቀበል አሸናፊነት መኾኑን ተናግረዋል። ይህን ለመረጡ አካላትም አመስግነዋል።
ሰላም የሁሉም ነገር መቋጫ መኾኑንም ገልጸዋል አሥተዳዳሪው። ሰላምን የመረጡ አካላት ሌሎች በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎችም የነሱን ሃሳብ እንዲከተሉ መሥራት እንዳለባቸው ነው የተናገሩት።
የደቡብ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፖርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መንበር ክፈተው የሰላምን ዋጋ በመረዳት ታሪካዊ ጠላት የደገሰውን ሴራ አክሽፎ ለዚህ መብቃት የትልቅነት ማሳያ ነው ብለዋል።
የ10ኛ ዕዝ አንድ ኮር ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ተሾመ ይመር የሰላም አማራጭን መቀበላችሁ አልረፈደም እንኳን ደህና መጣቹህ ብለዋል።
የኃይል አማራጭ የሰውን ልጅ ክቡር ሕይዎት ከመገበር ያለፈ ሊያመጣ የሚችለው ፋይዳ የለም ብለዋል። ለአማራ ሕዝብ ትልቅ ልማትን ማልማት እየተቻል የደረሰው ኪሳራ አሳዛኝ እንደኾነ ነው የገለጹት።
ነገር ግን ከዚህ በላይ ሊደርስ የሚችልን ጥቃት ሊያቆም የሚችል የጀግና ውሳኔ ላይ በመድረስ የተደረግው ስምምነት እንዳስደሰታቸው ነው የተናገሩት።
ሎሎች በጫካ ያሉ ታጣቂዎችም ይህን ትልቅ ዕድል በመረዳት መጥተው የሴረኞችን ሃሳብ ማክሸፍ አለባቸው ብለዋል።
የነፋስ መውጫ ቤተ ክህነት ሥራ አሥኪያጅ መምህር መሠረት ፀጋየ ለሰላም በመትጋት ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ገልጸዋል። አሁንም የመንግሥት የሰላም እጅ ሳይታጠፍ ሌሎች አካላት በፍጥነት ሥራውን ማከናወን አለባቸው ብለዋል።
ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ሼህ ደሴ ከተማው የሰላም አማራጭ አይተኬ ሚና አለው ብለዋል። በሃሳብ የበላይነት አምነው የመጡ ወንድሞችንም አመስግነዋል።
የገብረየ ክፍለ ጦር አዛዥ የኾኑት አዲሱ ደባልቄ የሕዝብ ጥያቄን ይዞ ጫካ ገብተው እንደነበር አንስቷል።
ይሁንና ጥያቄው በነበረው የኃይል አማራጭ የሚሳካ ባለመኾኑ ስምምነቱን ተቀብለን ገብተናል ብሏል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
