
ባሕር ዳር፡ ጥር 16/2018ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ “የሕግ የበላይነት እና አማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴዎች ለዘላቂ ሰላም እና ልማት” በሚል መሪ መልዕክት በጋራ ያዘጋጁት ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
በኮንፈረንሱ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ አማራ ክልል ለሰላም እና ለልማት ጉልህ ሚና የሚጫወቱ ባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓቶች እና የዳበሩ ባሕላዊ የሙግት መፍቻ ዘዴዎች ያሉት ስለመኾኑ አንስተዋል።
ክልሉ “ጥጋብ ካለበት ሀገር ይልቅ ዳኛ ያለበት ሀገር ይሻላል” የሚል እና ለሕግ የበላይነት መከበር ጽኑ ፍላጎት ያለው ሕዝብ መኖሪያ ነው ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
የባሕል ፍርድ ቤቶች በሕዝቡ ተፈላጊ ቢኾኑም ተገቢው ቦታ ሳይሰጣቸው መቆየቱንም ገልጸዋል። የዛሬው ኮንፈረንስ ባሕላዊ ፍርድ ቤቶችን በተገቢው መንገድ እና ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች ጋር በማጣጣም ለመጠቀም የሚያስችሉ ሃሳቦችን ለማንሸራሸር እንደሚረዳም ገልጸዋል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለችበት ጂኦስትራቴጅያዊ አቀማመጥ የተነሳ ቀላል የማይባሉ የውስጥ እና የውጭ ወጀቦችን አስተናግዳለች፤ አማራ ክልልም እንደ ኢትዮጵያዊነቱ የዚሁ ፈተና ገፈት ቀማሽ ኾኖ ቆይቷል ነው ያሉት።
አንዱን ፈተና ስናልፍ ሌላው ብቅ ማለቱ አማራጭ የፍትሕ ሥርዓቶቻችንን እንደገና እንድንፈትሽ አስገድዶናል ብለዋል።
መደበኛው ፍርድ ቤት ውሳኔን ከማስፈጸም አይሻገርም፤ ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ግን እርቅን ያወርዳሉ፣ ማኅበራዊ መስተጋብርንም እንደገና ያስተካክላሉ ነው ያሉት።
በመኾኑም ባሕላዊ ፍርድ ቤቶችን ከዘመናዊው ጋር በማሰናሰል በሀገር አቀፍ ደረጃም ልንጠቀምባቸው ይገባል ሲሉ አሳስበዋል። ይሕ ሲኾን ፍትሕ ይረጋገጣል ማኅበራዊ ሰላምም ይሰፍናል ነው ያሉት።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለያዩ ምክንያቶች መሣሪያ ባነሱ አካላት ዘመናዊውም ኾነ ባሕላዊ የፍትሕ ሥርዓቶች ተጎድተው መቆየታቸውን ጠቅሰዋል። ይህም አግባብ ባለመኾኑ ሊታረም እንደሚገባ አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ ሰረገላ በፍጥነት ወደፊት እየተሽከረከረ ነው፤ በጊዜ የሚሳፈሩት በጉዞው ይካተታሉ፤ በጊዜ የማይሳፈሩት ጉዞውን መሬት ላይ ኾነው ይመለከታሉ፤ ለማደናቀፍ የሚጥሩት ደግሞ በሀፍረት አንገታቸውን ስለሚደፉ ጉዞውንም ለማየት አይቻላቸውም ብለዋል።
“ወደፊት ከሚሽከረከረው የኢትዮጵያ ሰረገላ ጋር በአንድነት እንጓዝ” ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እንዳሉት አማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴዎች ለፍትሕ ተደራሽነት እንዲሁም ለዘላቂ ሰላም እና ልማትም ቁልፍ ሚና አላቸው። የዛሬው ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስም ከመደበኛው ፍርድ ቤት ጋር ስለሚኖራቸው ዘላቂ መስተጋብር በጋራ የምንመክርበት ነው ብለዋል።
ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሱ የክልሉን የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት ትራንስፎርሜሽን ውጤታማነት አመላካች እና በጋራ ለመሥራትም መልካም ጅማሮ ስለመኾኑ ገልጸዋል።
በየዕለቱ የሚያጋጥሙ የመብት እና ጥቅም ግጭቶችን ለመፍታት ከመደበኛው ፍርድ ቤት በተጨማሪ ለዘመናት ጥቅም ላይ ሲውሉ የነበሩ የዳበሩ ባሕላዊ ፍርድ ቤቶችንም መጠቀም ይገባል ብለዋል።
የክልሉ ፍርድ ቤቶች በሀገር አቀፍ ደረጃም ተምሳሌታዊ እና ሞዴል ተደርገው የሚወሰዱ እንዲኾኑ እየተሠራ ስለመኾኑም ጠቅሰዋል። “የፍርድ ቤቶች ድክመት የመንግሥትን ድክመት፤ ጥንካሬያቸው ደግሞ የመንግሥትን ጥንካሬ ከፍ የሚያደርግ እንደኾነ እናምናለን” ሲሉም ተናግረዋል።
ፍርድ ቤቶች የሪፎርም ሥራዎች ውጤታማ ኾነው እንዲቀጥሉ እና የሕግ ማሻሻያዎችም እንዲደረጉ የክልሉ መንግሥት በበጀትም በመደገፍ በልዩ ትኩረት እየሠራ ስለመኾኑም ገልጸዋል።
የሰላም ሚኒስትሩ መሐመድ እድሪስ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሱ የሕግ የበላይነት፣ አማራጭ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች፣ ዘላቂ ሰላም እና ልማት የሚዳሰሱበት በአይነቱ ልዩ መኾኑን ገልጸዋል።
ልማት የሰው ልጅ ዋነኛ ፍላጎት ነው፤ መልማት ደግሞ ከኑሮ እና ከተፈጥሮ ጋር ያለንን ቁርኝት የሚያሳምር ጉዳይ ነው ብለዋል። የምናልመውን ልማት እና ብልጽግና ለማምጣት ደግሞ ሰላምን ማረጋገጥ ቀዳሚው ተግባር ሊኾን እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ከንግግር ሊያልፉ የማይገባቸው ፍላጎቶች አያጋጩን፤ በሠለጠነ መንገድ ሊፈቱ የሚችሉ ጉዳዮች ጥልን ፈጥረው ልማቶቻችንን ወደኃላ አይጎትቱብን ብለዋል ሚኒስትሩ።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
