“አየር ኃይላችን አየራችን ብቻ ሳይኾን ፍላጎታችንንም የሚጠብቅ ይኾናል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

14

ባሕርዳር፡ ጥር 16/2018ዓ.ም (አሚኮ) አየር ኃይል 90ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት እያከበረ ነው።

አየር ኃይሉ ባለፉት ዓመታት ከፍ እና ዝቅ ብሎ በማገልገል ኢትዮጵያን መጠበቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አንስተዋል።

አየር ኃይሉ በአፍሪካም በሰላም አስከባሪነት በማገልገል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር ከኢትዮጵያውያን ውጭ ሌላ ግዴታ ያለበት የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚያው ልክ የመተግበርንም አስፈላጊነት ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል በርካታ ጀግኖች የሚፈጠሩበት ተቋም መኾኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህን ጀግኖች የበለጠ ለማብዛት የሰው ኃይል ላይም መሥራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ለብቁ ተዋጊ ኃይል ሀገራቸውን የሚወዱ እና የማይሰለቹ ባለሙያዎችን የማፍራት አስፈላጊነትን ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታትም የተጀመረው አየር ኃይልን የማጠናከር ሥራ ለሰው ኃይል ግንባታ ትኩረት መሰጠቱን ያመላክታል ብለዋል።

በየግንባሩ እና በየዘርፉ ለሀገር መቆም፣ መጽናት፣ መትጋት፣ መልፋት እና አይበገሬነትን ማሳየት እንደሚያስፈልግም ጠቅሰዋል። በልዩ ልዩ ዘርፎች የማይበገሩ ጀግኖችን ዕውን ማድረግ እንደሚገባም አንስተዋል።

በአፍሪካ ግንባር ቀደም የልማት እንቅስቃሴ እየተፈጸመ ያለው በኢትዮጵያ ነው። ባለፈው ዓመት 9 ነጥብ 2 በመቶ አድገናል፤ ዘንድሮም የ10 ነጥብ 3 በመቶ ዕድገትን ለማረጋገጥ እየሠራን ነውም ብለዋል።

የጠንካራ ኢኮኖሚ ባለቤት ቢኾኑም የመከላከያ ዘርፋቸውን ችላ ያሉ ሀገራት የገጠማቸውን አይተናል፤ ስለኾነም በሁሉም ዘርፍ መጠናከር እና መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲ፣ በፖለቲካ እና በመከላከያ አቅም መጠንከር የተከበረች ኢትዮጵያን ለትውልዱ ለማስረከብ ያለውን አስፈላጊነትም ጠቅሰዋል።

አየር ኃይል አጥንቱን ከስክሶ ድል ማስመዝገብ ያለፈበት መኾኑን ጠቅሰው ቴክኖሎጂን የመጠቀም አስገዳጅነትንም ትኩረት ሰጥተው አንስተዋል። ስለኾነም በቀጣይ አምስት ዓመታት የአሁን አቅማችን በእጥፍ ያድጋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለአብሮነት እና ለመማማር ትሠራለች። በዚያው ልክ ለጠላቶቻችን በራችን ዝግ መኾኑን ማሳወቅ ይገባል ነው ያሉት።

ለአብሮነት እና ልማት እንተባበራለን፤ ነገር ግን የኢትዮጵያን ሰላም እና ጥቅም ለማስከበር አንተኛም ነው ያሉት።

የአፍሪካ ትንሳኤ ምልክት ከምትኾን ሀገር ኢትዮጵያ ጋር ተስማምቶ እና ተባብሮ መሥራት ያስፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ውስጥ ብልጽግናን እናረጋግጣለን ብለዋል።

እንቅፋቶች ያበረቱብናል እንጂ አያስቆሙንም። ለዜጎቿ የምትጠቅም እና የምትመች ሀገር እና ዜጎቿ በይቅርታ የሚተቃቀፉባት ሀገር እንድትኾንም እንሠራለን ብለዋል።

“አየር ኃይላችን አየራችን ብቻ ሳይኾን ፍላጎታችንም የሚጠብቅ ይኾናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአየር ኃይል አባላትም ኀላፊነታቸውን እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ በትጋት እንዲወጡም አደራ ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleመዛግብት በአጭር ጊዜ ውሳኔ የሚያገኙበትን ዕድል ለመፍጠር በትኩረት እየተሠራ ነው።
Next article“ወደፊት ከሚሽከረከረው የኢትዮጵያ ሰረገላ ጋር በአንድነት እንጓዝ” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ