
ደብረ ብርሃን፡ ጥር 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባለፉት ስድስት ወራት የነበረውን የሥራ አፈጻጸም ገምግሟል፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዮሃንስ ወንድሙ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት እስከ ወረዳ ፍርድ ቤቶች ድረስ የአገልግሎት ጥራትን ታሳቢ ያደረጉ ተልዕኮዎች ተቀርጸው ተቋማቱ እየሠሩ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም የተገልጋይ እርካታ ለማምጣት በግማሽ በጀት ዓመት የተሠራው ተግባር የተሻለ አፈጻጸም የታየበት እንደነበር አስታውሰዋል።
ፍርድ ቤቶች በአጭር ጊዜ በተቀላጠፈ ሁኔታ ውሳኔ መሰጠት እንዲችሉ ሰፊ ሥራ መሠራቱን የከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል፡፡ በቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ የተቀላጠፈ የዳኝነት አገልግሎቱን ለመስጠት ተሞክሯልም ብለዋል፡፡
በከፍተኛ ፍርድ ቤቱ በኩል ባለፉት ስድስት ወራት 1 ሺህ 193 መዛግብት ከስድስት ወር በፊት ውሳኔ አግኝተው መዘጋታቸውን ገልጸዋል።
ጥራት ያለው ውሳኔ በመስጠት ረገድ ከመሻር፣ ማሻሻል እና ማጽናት አንጻር የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በቀጣይ ለማስተካከል ጠንካራ ውይይት መደረጉንም ተናግረዋል፡፡
ዳኞች ሥነ-ምግባርን በተከተለ እና ሙያዊ ኀላፊነታቸውን ከግምት ውስጥ ባስገባ መንገድ ሥራዎቻቸውን እንዲያከናውኑ ተገቢ ክትትል እና ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል፡፡
በጥቅሉ በግማሽ ዓመቱ በፍትሐ ብሔር እና በወንጀል ጉዳዮች 23 ሺህ 182 መዛግብት ቀርበዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 20 ሺህ ያህሉ መዛግብት እልባት አግኝተዋል ተብሏል፡፡
የአፈፃፀሙም ክንውን ከዕቅድ አንፃር 92 በመቶ መኾኑም ተጠቁሟል፡፡
ዘጋቢ፦ አበበች የኋለሸት
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
