በክልሉ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ኅብረተሰቡ ድጋፉን እንዲያጠናክር ተጠየቀ።

10

ባሕር ዳር፡ ጥር 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎‎‎የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ባለፉት ስድስት ወራት በተከናወኑ የተግባራት አፈጻጸም እና በቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ከዞን የፖሊስ መሪዎች ጋር መክሯል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር እና የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር አበበ ውቤ በክልሉ በወንጀል መከላከል ዘርፍ ሰፊ ሥራዎች ተከናውኗል ብለዋል።

በክልሉ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ለመከላከል በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን አንስተዋል። የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥም ከሌሎች የጸጥታ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ በመሥራት ውጤታማ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት።

በቀጣይም በክልሉ አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን፣ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እና ዘላቂ የወንጀል መከላከል ሥራዎችን ለመሥራት ኅብረተሰቡ ባለቤት ኾኖ ድጋፍ ማድረግ ይገባዋል ብለዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር አሳምነው ሙላት በዞኑ ማኅበረሰቡን ከጸጥታው ጎን እንዲሰለፍ በማድረግ የተሻለ ሰላም ማምጣት መቻሉን ገልጸዋል።

የጸጥታ መዋቅሩም የተሟላ ግንዛቤ ወስዶ በቁርጠኝነት ሰላም የማስከበር ሥራውን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ንጉሴ ሞገስ እንደተናገሩት እንደ ተቋም የተሠራውን ሪፎርም ተግባራዊ በማድረግ በዞኑ ውጤታማ የሕግ ማሥከበር ሥራዎች ተሠርተዋል። በዚህም በዞኑ አንጻራዊ ሰላም ማምጣት ተችሏል ብለዋል።

በቀጣይም ሕዝቡን በማሳተፍ እና በቅንጅት በመሥራት የተሟላ ሰላምን ለማረጋገጥ እንደሚሠራ ነው የተናገሩት።

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“በጋራ በመሥራት ውጤታማ መኾን እንደሚቻል ለጥምቀት የተሠራው ተግባር ማሳያ ነው” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው
Next articleበሕግ የበላይነት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።