
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 22/2012 ዓ.ም (አብመድ) የመፍትሔ ሐሳቦች ለክልሉ ካቢኔ ቀርበው ከጸደቁ በኋላ ሰነድ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ እንደሚገባ የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታውቋል፡፡
በአማራ ክልል በመንግሥት ድጎማ የሚቀርበው የዳቦ ዱቄት፣ አቅርቦትና ስርጭት በማኅበረሰቡና በዳቦ ቤቶች ቅሬታ ይነሳበታል፡፡ የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ከዳቦ አምራቾች ዘርፍ ማኅበራት ጋር በመሆን የችግሩን ክፍተት ለመለየት የዳሰሳ ጥናት አካሂዷል፡፡
በክልሉ በሚገኙ ሰባት የዞን ከተሞች ማለትም በባሕር ዳር፣ ደሴ፣ ወልዲያ፣ ኮምቦልቻ፣ ጎንደር፣ ደብረ ማርቆስና ፍኖተ ሠላም ከተማ አስተዳደሮች ጥናቱ ተደርጓል፡፡ ከ400 በላይ ዳቦ ቤቶችና ተጠቃሚዎች በጥናቱ ተሳትፈዋል፡፡
ለኅብረተሰቡ እየቀረበ ያለው የዳቦ ግራም መጠን ጉድለት እንዳለበት፣ የዳቦ ንጽሕና እና ጥራት ተጠብቆ እየተሸጠ እንዳልሆነ፣ ዳቦ ቤቶች ለሸማቹ ማኅበረሰብ ተገቢ አገልግሎት በመስጠት በኩል ጉድለት እንዳለባቸው፣ ኢ-ፍትሐዊ የስንዴ ዱቄት ክፍፍል (ስርጭት) መኖሩ፣ የዳቦ ዋጋ ተመን ለማምረት የሚያስፈልገውን ወጪ ታሳቢ ያላደረገና ነጋዴውን ለኪሳራ የሚዳርግ መሆኑ፣ የዳቦ ሽያጭ ዋጋ በተመኑ መሠረት እየተካሄደ አለመሆኑንና ሌሎች ችግሮችን ጥናቱ ተመልክቷል፡፡
መንግሥት እያቀረበ ያለውን የድጎማ የስንዴ መጠን ከፍ እንዲያደርግ፣ መንግሥት መጠኑን ማሳደግ የማይችል ከሆነ በአጠቃላይ ከድጎማ ቢወጣ፣ መንግሥት የዳቦ ዱቄት አቅርቦቱን ለሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ቢያሸጋግር፣ መንግሥት ልክ እንደ ሸገር ዳቦ በተመጣጣኝ ዋጋ ዳቦ ለኅብረተሰቡ የሚያቀርቡ ፋብሪካዎችን ቢከፍት፣ በትስስር ውስጥ ያሉ ዳቦ ቤቶች ዱቄት አየር በአየር እየሸጡ በመሆኑ ሁሉም ዳቦ ቤቶች ከትስስር እንዲወጡ ቢደረግ፣ የሕግ ማዕቀፍ ወጦ ሁሉም ዳቦ ቤቶች መብትና ግዴታቸውን እንዲወጡ ቢሆን፣ የአሠራር ቁጥጥር ሥርዓቱ እስከ ወረዳ ድረስ ቢዘረጋ፣ ለኅብረተሰቡ በነፃ ገበያና በትስስር ውስጥ ስላሉት ዳቦ ቤቶች ግንዛቤ በሰፊው ቢፈጠርለት፣ የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ መመሪያ ቁ. 05/2011 የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የንግድ ቢሮ ባለሙያዎች በዳቦ ቤት ትስስር ውስጥ እንዳይገቡ ቢከለክላቸውም በርካቶች በትስስር ውስጥ በመዘፈቃቸው ጥብቅ ቁጥጥር ቢደረግ፣ አሁንም በየወረዳው እየሠሩ የሚገኙ የንግድ ተቋማት መሪዎችና ባለሙያዎች የዱቄት አከፋፋዮችና ፋብሪካዎች ጋር አላስፈላጊ የጥቅም ግንኙነት በመሠረቱት ላይ ክትትል ተደርጎ ርምጃ ቢወሰድና ሌሎች ነጥቦች ጥናቱ መፍትሔ አድርጎ ያቀረባቸው ምክረ ሐሳቦች ናቸው፡፡
የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ቻላቸው ወርቁ ጥናቱ ሕዝቡ ያነሳው የነበረውን ችግር እውነታነት ማረጋገጡን አመላክተዋል፡፡ ከጥናቱ በመነሳትም የመፍትሔ ሐሳብ ለክልሉ ካቢኔ ቀርቦ ከጸደቀ በኋላ ሰነድ እንደሚዘጋጅ ኃላፊው አብራርተዋል፡፡
በሂደት በተወሰነ ወይም በአጭር ጊዜ መንግሥት ከድጎማ የሚወጣበት አግባብ መኖሩን አቶ ቻላቸው አስረድተዋል፡፡
ለአማራ ክልል ከፌዴራል መንግሥት 72 ሺህ 4 መቶ 51 ኩንታል ስንዴ በየወሩ ተመድቦለታል፡፡ ወደ ዱቄት ሲቀየር 53 ሺህ ኩንታል የሚሆን ነው፡፡
ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡