“በጋራ በመሥራት ውጤታማ መኾን እንደሚቻል ለጥምቀት የተሠራው ተግባር ማሳያ ነው” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው

8

ጎንደር፡ ጥር 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎‎‎የጎንደር ከተማ አሥተዳደር የፓርቲ፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ተግባራት የሥድስት ወራት አፈጻጸም ግምገማ አካሂዷል።

‎በውይይቱ ባለፉት ወራት የእገታ ወንጀልን መከላከል መቻሉ እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን አጠናክሮ ማስኬድ መቻሉ በጥንካሬ የተነሱ ጉዳዮች ናቸው።

የሴቶችን ተሳትፎ በሁሉም ዘርፍ አለማደግ እና ተጠያቂነት አለማስፈን ደግሞ ከተማ አሥተዳደሩ በአፈጻጸሙ ያልተሻገራቸው ተግባራት እንደኾኑ ተነስተዋል።

‎የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ባለፉት ሥድስት ወራት በተሠራው የሰላም ተግባር ከተማዋ ወደቀደመ ሰላሟ ተመልሳለች ብለዋል። የተሠራው እና እየተሠራ ያለው የኮሪደር ልማት ጎንደርን ልዩ ውበት እና ገጽታ አጎናጽፏታል ነው ያሉት።

‎በጋራ መሥራት ውጤታማ መኾን እንደሚቻል ለጥምቀት የተሠራው ተግባር ማሳያ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ጎንደር ከተማን የተሻለች ከተማ አድርጎ ለኢትዮጵያ ምሳሌ ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል።

‎የሥራ ኀላፊዎች መልካም አሻራ አሳርፈው እንዲያልፉም ጠይቀዋል።

‎በችግር ውስጥ ኾኖ በርከት ያሉ ሥራዎች መሠራታቸውን የተናገሩት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋ መኮንን ናቸው። ‎የመሪዎችን የአስተሳሰብ ጥራትን ማሳደግ ተችሏልም ብለዋል።

‎ለቀጣይ ምርጫ ዝግጅት እየተደረገ ነው ያሉት ኀላፊው ተፎካከሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ እንደሚሠራም ተናግረዋል።

‎በውይይቱ አሚኮ ያናገራቸው የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ማሪያም ካሳሁን የጎንደርን ባሕል፣ ወግ እና ቅርስን ለማስተዋወቅ በርከት ያሉ ሥራዎች መሠራቱን አስረድተዋል።

በተሰራው ተግባርም አመርቂ ውጤት ተገኝቷል ብለዋል።‎በቀጣይም የጎብኝዎችን ቁጥር ለማሳደግ ይሠራል ነው ያሉት።

‎በተሠራው ሕግ የማስከበር ተግባር እገታ እና የሥርቆት ወንጀልን መከላከል ተችሏል ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ አለልኝ ዓለም ናቸው።

‎የጎንደር ከተማ ሰላም ዘላቂ እንዲኾን ተቋማቸው ተግቶ እንደሚሠራም ተናግረዋል።

‎የኑሮ ውድነቱን ማረጋጋት፣ የወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራን ማሳደግ እና ሕገ ወጥ ንግድን መከላከል በቀጣይ ሊሠራባቸው የታቀዱ ተግባራት እንደኾኑ በመድረኩ ተገልጿል።

መልካም አፈጻጸም ለነበራቸው ተቋማት እና የሥራ ኃላፊዎችም የምሥጋ እና የቁሳቁስ ድጋፍ ተበርክቶላቸዋል።

ዘጋቢ:- አዲስ ዓለማየሁ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየአማራን ሕዝብ በማንኛውም መስክ ለመካስ እና ለማገልገል ቁርጠኞች መኾናቸውን የቀድሞ ታጣቂዎች ገለጹ።
Next articleበክልሉ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ኅብረተሰቡ ድጋፉን እንዲያጠናክር ተጠየቀ።