
ደብረ ብርሃን፡ ጥር 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ብርሃን ከተማ ተሃድሶ ሥልጠና ማዕከል የሰሜን ሸዋ ዞን እና የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የቀድሞ ታጣቂዎች የተሃድሶ ሥልጠና ማጠቃለያ መርሐ ግብር ተካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ከዚህ በፊት የሄዱበት መንገድ ትክክል አለመኾኑን ከተሰጣቸው ሥልጠና መረዳታቸውን ሰልጣኞቹ ተናግረዋል።
የአማራን ሕዝብ በማንኛውም መስክ ለመካስ እና ለማገልገል ቁርጠኞች እንደኾኑም ጠቁመዋል።
በግጭቱ የአማራ ሕዝብ ማኅበራዊ ሕይዎት ለከፋ ቀውስ ተዳርጓል ያሉት ሠልጣኞቹ ከዚህ በኋላ ሊቆም እንደሚገባውም ገልጸዋል፡፡
ጫካ ያሉ ወንድሞችም ምርጫቸውን ሰላም እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በማጠቃለያ መርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው የሥራ መመሪያ የሰጡት የአማራ ክልል ሚሊሻ ኮሚሽን ኮሚሽነር አስቻለ አላምሬ ግጭቱ በሕዝብ እና በመንግሥት የተጀመሩ ልማቶችን ማስቀጠል እንዳልተቻለ በመረዳት ከዚህ በኋላ ባለው ጊዜ ሕዝብን ለመካስ በቁርጠኝነት ለሰላም እና ልማት በጋራ መቆም ይገባል ብለዋል።
በሥልጠናው ሕዝብ እና ሀገርን ለማገልገል የሚያስችል ቆይታ መደረጉን የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ደጀኔ ልመንህ ጠቅሰዋል።
የቀድሞ ታጣቂዎቹ በቀጣይም ወደ ማኅበረሰቡ ሲቀላቀሉ የያዙትን ዕውነታ እና ቁርጠኝነት በተግባር እንዲያሳዩ አሳስበዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት በጫካ ያሉ ታጣቂዎችም ሰላምን እንዲከተሉ ማድረግ እና በሕዝብ ውስጥ ሰላም እና ልማትን ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
በግጭት ምክንያት ዞኑ ሲፈተን እንደነበር ያስታወሱት የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መካሻ ዓለማየሁ በፌዴራል መንግሥት ከተያዙ 13 ፕሮጀክቶች ውስጥ ብዙዎቹ በጸጥታ ችግር መቆማቸውን አንስተዋል።
ወደ ሰላም መምጣት የተዘጉ በሮችን የሚከፍት፣ ሰላም እና ልማትን ለማስቀጠል የሚያስችል በመኾኑ የዞኑ አሥተዳደር ይህ የሰላም መንገድ ይበልጥ እንዲሳካ ይሠራል ብለዋል።
በብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የሥልጠና ዳይሬክተር ብርሃኑ ተስፋዬ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ81 ሺህ በላይ የቀደሞ ታጣቂዎች ሠልጥነው ወደ ማኅበረሰቡ መቀላቀላቸውን ገልጸዋል።
ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተው ለገቡ የቀድሞ ታጣቂዎች የማቋቋሚያ እና ከሕዝብ ጋር ተቀላቅለው እንዲገቡም ክትትል እንደሚደረግ ተናግረዋል።
በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት አዛዥ ኮሎኔል አደራጀው ሰረበ በሕዝብ እና በሀገር ላይ የመጣ ጠላት ኢትዮጵያን አሸንፎ እንደማያውቅ መታወቅ አለበት ነው ያሉት፡፡
ጫካ የሚገኙ ኃይሎችም ከሕዝብ እና ከመንግሥት የተደረገላቸውን ጥሪ በመቀበል ወደ ሰላም ቢመጡ የተሻለ ምርጫ መኾኑን ገልጸዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የሀገር ሽማግሌ አቶ አርጋው ኃይለመስቀል የገጠመው የሰላም እጦት ችግር በመወያየት መፍታት ይጠይቃል ብለዋል።
ለማኅበረሰቡ ሲባል የተጀመረውን የሰላም ምርጫ ሁሉም ሊጠቀምበት ይገባል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
