በከተማ እና በወረዳ አንድ የማኅበረሰብ መድኅኒት መሸጫ እንዲኖር እየተሠራ ነው።

8

ባሕር ዳር፡ ጥር16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዜጎች ለጤና አገልግሎት የሚከፍሉት ገንዘብ በማጣት ሊድን በሚችል ህመም እየተሰቃዩ፤ ላልተፈለገ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስም ይጋለጣሉ።

ይህንን ቀውስ ለመቅረፍ በኢትዮጵያ የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን አገልግሎት ሥርዓት ተዘርግቶ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ ።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሲስተር ክሽን ወልዴ በአማራ ክልል ለማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን አገልግሎት እስካሁን ከ7 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ 5 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ መሠብሠብ መቻሉን ተናግረዋል። አፈጻጸሙም 80 ነጥብ 4 በመቶ መኾኑን ነው የተናገሩት።

በገቢ አሰባሰቡ ከአቅም በላይ የኾነ እና የጎላ ችግር እንዳልገጠመ የተናገሩት ኀላፊዋ የጤና ጉዳይ ቀጠሮ ሊሰጠው እንደማይገባ ተናግረዋል። ማኅበረሰቡ ፈልጎ እና በፍቃደኝነት የማኅበረሰብ የጤና መድኅን አገልግሎት ክፍያ እየከፈለ እንደኾነም አንስተዋል።

አሚኮ ዲጅታል ሚዲያ ከማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻል አኳያ ላነሳላቸው ጥያቄም ሰፊ ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል።

በአብነትም ቀደም ሲል በሆስፒታል ደረጃ ሢሠራ የነበረ በቀዶ ጥገና ሕክምና የታገዘ የእናቶች የወሊድ አገልግሎት አሁን ላይ በብዙ ጤና ጣቢያዎች እንዲጀመር መደረጉን ጠቅሰዋል።

ጤና ጣቢያዎች ላይ ያልነበረ በአልትራሳውንድ የሕክምና መሳሪያ የታገዘ የሕክምና አገልግሎት እንዲኖር መደረጉንም ጠቁመዋል።

በደብረ ብርሃን፣ በወልዲያ፣ በደብረ ታቦር፣ በደብረ ማርቆስ እና በባሕር ዳር ከተማ ደግሞ በሲቲስካን የሕክምና መሣሪያ የታገዘ የሕክምና አገልግሎት እንዲኖር መደረጉንም ተናግረዋል። በቀጣይ ደግሞ በሌሎች ከተሞች እንዲጀመር ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።

በክልሉ የመጀመሪያ የኾነ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የሚባለው በኤም አር አይ የሕክምና መሳሪያ የታገዘ የሕክምና አገልግሎት በፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለማስጀመርም እንቅስቃሴ እየተደረገ መኾኑን ጠቅሰዋል።

“የሚገጥመውን የመድሃኒት እጥረት ለመቅረፍ” ደግሞ በክልሉ ቁጥራቸው 60 የሚደርሱ የማኅበረሰብ መድሃኒት ቤቶች በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን ተናግረዋል። በቀጣይ በአንድ ከተማ አንድ እና በአንድ ወረዳ አንድ የማኅበረሰብ መድኅኒት መሸጫ እንዲኖር እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።

በመጨረሻም የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን አገልግሎት ለመጠቀም የሚያስችለውን ደብተር ያላደሱ ነባር አባላት እንዲያድሱ አሳስበዋል። አባል ያልኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችም የጤና መድኅን አገልግሎት ለማግኘት የሚያስችለውን ክፍያ በመክፈል አባል እንዲኾኑ ጥሪ አቅርበዋል።

‎የጎንደር ከተማ ነዋሪ የኾኑት አስር አለቃ ደበበ ደሳለኝ ቀደም ሲል በግላቸው ሕክምና ሲከታተሉ ለሕክምና አገልግሎት የሚያስፈልጋቸው ገንዘብ ከፍተኛ በመኾኑ በአግባቡ ሕክምናቸውን ለመከታተል ተቸግረው እንደነበር ነግረውናል።

ለከፍተኛ ወጭ ተዳርገው እንደነበርም አስታውሰዋል። የጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚ ከኾኑ በኋላ ደግሞ ሕክምናቸውን በአግባቡ እየተከታተሉ እንደኾነ ነግረውናል።

የማኅበረሰብ የጤና መድኅን አገልግሎት ከአቅም በላይ ከኾነ የሕክምና ወጭ እንደታደጋቸውም ጠቅሰዋል።

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን የሦስተኛ ዙር የቀድሞ ተዋጊዎች የምረቃ መርሐ ግብር በኮምቦልቻ ከተማ ተካሂዷል።
Next articleየአማራን ሕዝብ በማንኛውም መስክ ለመካስ እና ለማገልገል ቁርጠኞች መኾናቸውን የቀድሞ ታጣቂዎች ገለጹ።