
ደሴ: ጥር 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን በሀገሪቱ በተለያዩ ክልሎች ሲንቀሳቀሱ የነበሩ እና ከግጭት ወጥተው ወደ ሰላሞ አማራጭ የመጡ የቀድሞ ተዋጊዎችን የተሃደሶ ሥልጠና ሰጥቷል።
በቀጣይም ወደ ማኅበረሰቡ መልሶ በማቀላቀል ወደ ሰላማዊ ሕይዎት እንዲመለሱ እና የሰላም እና የልማት አጋር እንዲኾኑ እየሠራ ይገኛል።
በአማራ ክልል የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ለማጽናት መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ደርጅት (አፋሕድ) ከፍተኛ መሪዎች ከክልሉ መንግሥት ጋር የሰላሞ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።
እነዚህ ከፍተኛ መሪዎች በምረቃን መርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተዋል።
በሰላም ስምምነቱ መሠረትም ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን እነዚህን መሪዎች እና አባሎች ይፋዊ የጦር መሣሪያ ርክክብ ያደረጉ ሲኾን በተጨማሪም የተሃድሶ ሥልጠና የወሰዱ የቀድሞ ተዋጊዎችን አስመርቋል።
ባለፉት ዓመታት በክልሉ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን የጠቀሱት ደግሞ የአፋሕድ የውጭ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ ናቸው።
የክልሉ ሕዝብ ካለበት ነባራዊ ጫና እንዲወጣ የሰላምን መንገድ መርጠናል ያሉት ካፒቴን ማስረሻ በቀጣይም ሕዝቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች መንግሥት እንዲመልስ እና በጫካ ያሉትንም ወደ ሰላም እንዲመጡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የአፋሕድ ምክትል ሊቀመንበር እና ወታደራዊ አዛዥ የነበሩት ኮሎኔል ፋንታው ሙሐባ የአማራ ሕዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ለማስመለስ ነፍጥ ማንሳት መፍትሔ አለመኾኑን ገልጸዋል። ጥያቄዎችን በመወያየት ለማስመለስ እንደሚሠሩም ተናግረዋል።
በአማራ ክልል ባለፉት ሁለት ዓመታት በነበረው ግጭት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ውጭ ማድረጉን የተናገሩት የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መሐመድአሚን የሱፍ ናቸው።
የሰላም አማራጭን በመምረጣችሁ ተማሪዎች ዳግም ወደ ትምህርት እንዲመለሱ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
ተሃድሶ የወሰዱት የቀድሞ ታጣቂዎች አምራች ወጣቶች በመኾናቸው ከተማ አሥተዳደሩ አስፈላጊውን የሥራ ዕድል ለመፍጠር ዝግጁ መኾኑንም ከንቲባው ጠቁመዋል።
አለመግባባቶችን እና ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚገባ ያነሱት ደግሞ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጄኔራል ደርቤ መኩሪያ ናቸው። እኩይ ሴራ ያላቸውን አካላት ተግባር ለማክሸፍ በአንድነት መሥራት ይገባል ነው ያሉት።
በአማራ ክልል ከ3 ሺህ 200 በላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ከባለፉት ዓመታት ጀምሮ ከ83 ሺህ በላይ የቀድሞ ተዋጊዎች የሰላምን አማራጭ መቀበላቸውን ምክትል ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።
የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) ወጣቶች ለሀገር ግንባታ የሚያበረክቱት ድርሻ ጉልህ በመኾኑ ይህንን በመረዳት ወደ ሰላም ለመጡ የቀድሞ ተዋጊዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ሌሎች ሀገራት ከነበሩበት የጦርነት አዙሪት ወጥተው ለሀገራቸው ዕድገት መሠረት የጣሉት በውይይት በመኾኑ የነዚህን ሀገራት መልካም ተሞክሮ መውሰድ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ሰልሀዲን ሰይድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
