
ባሕር ዳር: ጥር 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያውን ስድስት ወራት የዕቅድ አፈጻጸም እየገመገመ ነው።
በአፈጻጸም ግምገማው የመክፈቻ መርሐ ግብር ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ (ዶ.ር) በክልሉ ያጋጠሙ የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት መደረጉን አንስተዋል።
ተቋማዊ ሪፎርምን በማጠናከር፣ “ጠንካራ የፖሊስ ሠራዊት በመገንባት፣ የክልሉን ሰላም ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚያስችሉ ሥራዎችን ተከናውነዋል” ብለዋል። እነዚህ ተግባራትም ውጤታማ መኾናቸውን ገልጸዋል
በዚህም በወንጀል መከላከል፣ በወንጀል ምርመራ፣ በአሥተዳደር ልማት እና በተቋም ግንባታ ተስፋ ሰጭ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል። ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ ስኬታማ የሪፎርም ተግባራት በመከናወናቸውም የተቋሙን የመፈጸም አቅም ከፍ እንዲል አድርጎታል ነው ያሉት።
በተሠሩት የሪፎርም ሥራዎችም ጠንካራ አደረጃጀት እና የአሠራር ሥርዓት መዘርጋቱ ውጤታማ ተቋማዊ የገጽታ ግንባታ መሠራቱ፣ ዲጅታላይዜሽንን ተግባራዊ በማድረግ ግብዓቶችን ማሟላት መቻሉን ለአብነት አንስተዋል።
ከሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ጋርም ጠንካራ የሕግ ማስከበር ሥራዎች በመከናወናቸው የተሻለ ሰላም ማምጣት መቻሉን ጠቁመዋል። የሠራዊቱን አቅም ለመገንባት የሚያስችሉ የሰው ኃይል ግንባታ ላይም ትኩረት ተደርጎ መሠራቱን ገልጸዋል።
የተገኙ ውጤቶችን አጠናክሮ በማስቀጠል እና ክፍተቶችን ገምግሞ በማስተካከል እንዲሁም በመሙላት በቀጣይ ለሚከናወኑ ተግባራት መዘጋጀት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
