
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 22/2012 ዓ.ም (አብመድ) የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ዛሬ ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም ከቻይና ስቴት ካውንስልና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዩ ጋር በስልክ ተወያይተዋል፡፡
ሁለቱ ሚኒስትሮች በነበራቸው የስልክ ውይይት በሁለትዮሽ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ ሁለቱ አገራት ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ማጠናከር በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል። አቶ ገዱ የቻይና መንግስት ”በቤልት እና ሮድ ኢንሸቴቭ” አማካኝነት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት የሚያስችል የቻይና አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ እና የሚኒስትሮች ውይይት በቅርቡ በተሳካ ሁኔታ ማካሄድ በመቻላቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል። ወረርሽኙን ለመግታት ቻይና ለኢትዮጵያ እያደረገች ላለው ድጋፍም ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ኢትዮጵያ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ከቻይና ጋር የጀመረችውን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥልም አቶ ገዱ ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ሰሞኑን በአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀመንበር ሲርል ራማፎሳ ሰብሳቢነት የተካሄደውን አስቸኳይ የመሪዎች ጉባኤ ቢሮ ስብሰባና ውሳኔ በተመከተም ሚኒስትሩ ገለጻ አድርገዋል። መሪዎቹ የናይልና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ የአፍሪካ ጉዳይ በመሆኑ ከአፍሪካ የሚመነጭ መፍትሄ እንደሚያስፈልገው መስማማታቸውን፣ በዚሁ መሠረት በግድቡ ሙሊት እና አሰተዳደር ላይ የሚደረገው ድርድር በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት እንደሚጠናቀቅ መስማማታቸውንም አቶ ገዱ አስረድተዋል።
የአፍሪካ ኅብረት ጉዳዩን መመልከት መጀመሩን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እንዲገልጥ መወሰኑንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡ ጉዳዩ በአፍሪካ ኅብረት በኩል መታየት በጀመረበት አግባብ እንዲፈታ ቻይና ድጋፏን እንድታደርግ አቶ ገዱ መጠየቃቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡
የቻይና ስቴት ካውንስልና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዩ በበኩላቸው ቻይና ከኢትዮጵየ ጋር ላላት ግንኙነት ልዩ ትኩረት እንደምትሰጥ ገልጸዋል። ትብብሯን ይበልጥ አጠናክራ እንደምትቀጥልም አስረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ያላቸውን ልዩነት በውይይት እንዲፈቱ ቻይና ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥልም ዋንግ ዩ አረጋግጠዋል።