በአለፋ ወረዳ የታጠቁ አካላት የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀበሉ።

59

ባሕር ዳር: ጥር 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በማኅበራዊ ድረ ገጹ እንዳስነበበው በማዕከላዊ ጎንደር ዞን አለፋ ወረዳ በተሳሳተ መንገድ ታጥቀው በጫካ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የታጣቂ ቡድን አባላት መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀብለዋል።

እነዚህ የታጠቁ አካላት ላለፉት ጊዜያት በጫካ ውስጥ የነበራቸውን እንቅስቃሴ በማቆም፣ የአካባቢውን ሰላም እና መረጋጋት ለማረጋገጥ ከመንግሥት ጋር በትብብር ለመሥራት ወስነዋል።

የሰላም አማራጩን የተቀበሉ የታጣቂ ቡድን አባላት በጫካ ውስጥ ሲጠቀሙባቸው የነበሩ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን እና ተተኳሾችን ለሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት አስረክበዋል።

ይህ የጦር መሳሪያ ርክክብ ታጣቂዎቹ ለሰላም ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ሲኾን በአካባቢው ሕገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመግታት እና የዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅ ትልቅ እገዛ ያደርጋል።

የታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ ሕይወት መመለስ በአለፋ ወረዳ እና በአካባቢው ለሚገኙ ነዋሪዎች አስተማማኝ መረጋጋትን የሚፈጥር ነው ተብሏል።

መንግሥት ወደ ሰላም የተመለሱ አካላት ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እንዲቀላቀሉ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ እና አሁንም በጫካ ለሚገኙ ሌሎች አካላት የሰላም ጥሪው ክፍት መኾኑን አረጋግጧል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ግጭት ችግርን ከማራዘም ውጭ ለውጥ እንደማያመጣ ተረድተናል” የሰላም አማራጭን የተከተለው ወጣት
Next articleየሰላም ጥሪን የተቀበሉ የአፋህድ መሪዋች በአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ሥራዋችን እየጎበኙ ነዉ።