
ባሕር ዳር: ጥር 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ባለፉት ዓመታት በተከሰተው የጸጥታ ችግር ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ደርሷል፤ እየደረሰም ይገኛል።
የተከሰተውን የሰላም ችግር ለመፍታት ከሕግ ማስከበር ባለፈ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሢሠራ ቆይቷል። በተሠራው ተግባርም በርካታ የታጠቁ ኃይሎች የሰላም አማራጭን እንዲከተሉ መደረጉን የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ መረጃ ያሳያል።
በደቡብ ጎንደር ዞን ሊቦ ከምከም ወረዳ ሲንቀሳቀሱ ቆይተው የሰላም አማራጭን ከተከተሉት ውስጥ ሙላት አበባው ይገኝበታል። ወጣት ሙላት 2015 ሰኔ ወር ላይ “የአማራ ሕዝብ የሕልውና ችግር ውስጥ ወድቋል” በሚል ወደ ጫካ እንደገባ ነግሮናል።
በተፈጠረው ግጭት ምክንያትም የተሳታፊ ወጣቶች እና የንጹሐን ሕይወት ማለፉን፣ በተለያዩ የሕዝብ መገልገያ ተቋማት ላይ ደግሞ ውድመት መድረሱን ነው የገለጸው። ማኅበረሰቡ ለዘረፋ እና ሌሎች ችግሮች መጋለጡንም ገልጿል።
ግጭቱ የክልሉን ሕዝብ ችግር ከማራዘም ያለፈ ፋይዳ እንደሌለው በመረዳት ከሚመራቸው 30 ወጣቶች ጋር የሰላም አማራጭን መከተላቸውን አንስቷል።
አሁን ላይ አካባቢያቸውን ተቀናጅተው እየጠበቁ መኾኑንም ተናግሯል። በቀጣይ የማኅበረሰቡ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ እና ሌሎች ያልገቡ ወጣቶችም የሰላም አማራጭን እንዲከተሉ እንደሚሠሩ ነው የገለጸልን።
መንግሥትም ችግሮች በሰላም እንዲፈቱ የጀመረው አማራጭን ይበልጥ ሊያሰፋ ይገባል ነው ያለው። ወጣቶች ወደ ሥራ የሚገቡበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚገባም ጠይቋል።
ባለፉት ወራት በክልሉ ሰላምን ለማረጋገጥ በተሠራው ሥራ በርካታ የታጠቁ ኀይሎች የሰላም አማራጭን መከተላቸውን የተናገሩት ደግሞ የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።
የሰላም አማራጭን ለተከተሉ ቡድኖች በተለያዩ ማዕከላት ሥልጠናዎች እየተጡ መኾኑን ገልጸዋል።
በተለይም ደግሞ የታጣቂ ቡድኑ መሪዎች ወደ ሰላም መምጣት ጥያቄዎችን በውይይት እና በዴሞክራሲያዊ መንገድ መፍታት አማራጩ መንገድ መኾኑን ያሳያል ብለዋል።
አሁን ላይ በክልሉ በተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም ክልሉ ያለውን እምቅ ሀብት በተሟላ መንገድ እንዲያለማ ዕድል መፍጠሩን አንስተዋል።
ሌሎች ቡድኖችም አሉኝ የሚሏቸውን ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ ነው የገለጹት። ማኅበረሰቡም ለሰላም እያበረከተ ያለውን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
