
ደሴ: ጥር 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “ዘመናዊ የገበያ መሠረተ ልማት ለውጤታማ የንግድ ሥርዓት” በሚል መሪ መልዕክት የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያው 6 ወራት የሴክተር ጉባኤ የእቅድ አፈፃፀም ግምገማ መድረክ በደሴ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) በንግድ ሥርዓት ላይ እየታየ ያለው ለውጥ በጋራ ከሠራን ለውጥ ማምጣት እንደምንችል ማሳያ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ዘመናዊ የገበያ መሠረተ ልማት ለማስፋፋት ሥራዎችን እያከናወኑ መኾኑን ያነሱት አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) ለውጦቹም አበራታች መኾናቸውን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ዘመናዊ የግብይት ማዕከል በመገንባት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የሚሠራው ሥራ የሚበረታታ እና ለሌሎች ክልሎች ተሞክሮ የሚኾን ነው ያሉት የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ ( ዶ.ር) ተሞክሮው ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
ባለፍት ስድስት ወራት የኑሮ ውድነት እና የዋጋ ግሽበትን ወደ ነጠላ አሐዝ ለማውረድ በተሠራው ሥራ ወደ 9 ነጥብ 7 በመቶ ማውረድ ተችሏል ያሉት ሚንስትሩ ይህም የተሳካው በብዙ ባለድርሻ አካላት ርብርብ መኾኑን አንስተዋል።
ለ1 ነጥብ 86 ሚሊየን ግለሰቦች በኦንላይን የንግድ ፈቃድ እድሳት ለመስጠት ታስቦ ለ2 ነጥብ 3 ሚሊየን ሰዎች እድሳት መሰጠቱንም ገልጸዋል።
ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች ባለፉት ስድስት ወራት 4 ነጥብ 42 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 5 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር ማሳካት መቻሉንም ሚኒስተሩ ተናግረዋል።
በመድረኩ ኹሉም ክልሎች ባለፉት ስድስት ወራት ያከናወኑትን ተግባር አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- አበሻ አንለይ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
