
ባሕርዳር፡ ጥር 14/2018ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን በኢትዮጵያ ብሎም በአማራ ክልል በተለይ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ አለመቀናጀት በአካባቢ ሥነ-ምህዳር እና በሕዝብ ጤና ላይ ጉዳት እያስከተለ መምጣቱን ገልጿል።
ባለሥልጣኑ ይህንን ሁኔታ ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እንዲሁም የተቀናጀ ብሎም ዘላቂ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ ሥርዓት ለመዘርጋት በ1383/2017 በወጣው አዋጅ ላይ የግንዛቤ እና የምክክር መድረክ አካሂዷል።
በምክክሩም አዋጁን በመተግበር ረገድ ክፍተቶች ይስተዋላሉ ነው የተባለው፡፡ የአማራ ክልል የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ኀላፊ በልስቲ ፈጠነ በመድረኩ ላይ እንዳሉት ከከተሞች መስፋፋት እና ፈጣን ዕድገት ጋር ተያይዞ የሚመረተው ደረቅ ቆሻሻ በትክክል ካልተያዘ በአካባቢ ላይ ብቻ ሳይኾን በሰዎች ጤና ላይም ከባድ አደጋ ያመጣል ብለዋል።
መንግሥት የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ በአዋጅ ቁጥር 1383/2017 ዓ.ም ቢያወጣም እስካሁን ሥራ ላይ አልዋለም ነው ያሉት።
አዋጁ በሕግ ደረጃ መኖሩ ብቻ በቂ አይደለም፤ ሕጉን ተግባራዊ ለማድረግ የሁሉም አካል ተሳትፎ እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል።
ማንኛውም ዜጋ በተመቻቸ እና ንፁህ በኾነ ቦታ የመኖር መብት አለው ያሉት ምክትል ኀላፊው በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት ከ950 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ የፕላስቲክ ቆሻሻ እና ከ7 ሺህ 500 ሜትር ኪዩብ በላይ የደረቅ ቆሻሻ የማስወገድ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ከ7 ሺህ 500 ኪሎ ሜትር በላይ የዲሽ ቦይ ጠረጋ ተካሄዷል ነው ያሉት።
በመጭዎቹ ዓመታት በገጠርም ኾነ በከተማ የሚኖረው የማኅበረሰብ ክፍል ንፁህ እና ማራኪ አካባቢን ለመፍጠር የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መሥራት እንደሚገባ ነው ያብራሩት።
የአማራ ክልል ምክር ቤት የግብርና እና የአካባቢ ጥበቃ ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ ከፍያለው ሙላቴ አሁን በከተማዋ የሕዝብ ቁጥር ጨምሯል፣ ኢንዱስትሪዎችም ተስፋፍተዋል ነው ያሉት።
በዚህ አካባቢ የሚፈጠረው ቆሻሻ ሀገርን እየበከለ ትውልድን እያጠፋ ይገኛልም ብለዋል። ቆሻሻን እንደ ቆሻሻ በማየት ትኩረት መስጠት ካልተቻለ በአጭር ጊዜ የሚፈለገውን ግብ ማሳካት አይቻልም ነው ያሉት።
ቆሻሻን መልሰን በመጠቀም የሥራ ዕድል በመፍጠር ለዜጎች ሃብት መኾኑን የማስገንዘብ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።
ሕጉን መሠረት አድርጎ የሚንቀሳቀስ ማኅበረሰብ በመፍጠር ዘላቂ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ ሥርዓት መገንባት እንደሚገባም አስረድተዋል።
የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ ችግር የአንድ ተቋም ብቻ ኀላፊነት ሳይኾን የማኅበረሰብ፣ የከተማ አሥተዳደሮች እና የግሉ ዘርፍ የጋራ ግዴታ መኾኑንም ጠቁመዋል።
አዋጁ ከጥር 23/2018 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚኾንም ተገልጿል።
ዘጋቢ:-ሰናይት በየነ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
