
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 22/2012 ዓ.ም (አብመድ) ሁለት አሜሪካ ሴናተሮች አሜሪካ በሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ ገለልተኛ አቋም እንድትይዝ በደብዳቤ መጤቃቸው ተሰምቷል፡፡
ሴናተር ኮሪ ቡከር እና ሴናተር ክርስቶፎር ኩንስ ለአሜሪካ የግምጃ ቤት ኃላፊ ስቴቨን መኑሸን በፃፉት ደብዳቤ ዩናይትድ ስቴትስ በሕዳሴ ግድብ ላይ በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ መካከል እየተደረገ ባለው ድርድር የያዘችው አቋም እንዳሳሰባቸው አስታውቀዋል፡፡ በመሆኑም በድርድሩ ላይ ራሷን ገለልተኛ እንድታደርግ አሳስበዋል። ሴናተሮቹ ከዚህ ቀደም በአሜሪካ ተረቅቆ ለፊርማ የቀረበው ስምምነት ለግብፅ የወገነ መሆኑን በመጥቀስ ኢትዮጵያ አለመፈረሟን አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያ በግድቡ ላይ ሲደርግ የነበረው ድርድር በስምምነት ተቋጨም አልተቋጨም ግድቡን በያዘችው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ውኃ እንደምትሞላ መግለጿን ተከትሎ በአካባቢው ውጥረት መፈጠሩንም አመልክተዋል፡፡ የግድቡ ግንባታ እየተጠናቀቀ እና የሁለቱ ሀገራት ተቃርኖ አየሰፋ በመጣበት በዚህ ወቅት ዩናይትድ ስቴትስ ሁኔታውን ልታበርድ ይገባል ማለታቸውን ፋብኮ ዘግቧል፡፡ ሆኖም በጉዳዩ ላይ አሜሪካ ገለልተኛ ባለመሆኗ ይህንን ውጥረት የማብረድ ሚና መጫወት እንዳትችል እንዳደረጋት ሴናተሮቹ አስረድተዋል።
ጉዳዩ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት መሄዱን ኢትዮጵያ እና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በመቃወማቸው ምክር ቤቱ ጉዳዩን ለመመልከት ተመራጭ ቦታ አለመሆኑንም ነው ያመለከቱት። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ለኢትዮጵያ በሁለትዮሽም ሆነ በሦስትዮሽ መንገዶች የሚደረጉ እርዳታዎች ወይም ድጋፎችን ለማገድ መንቀሳቀስ በአካባቢው ላይ በሚገኘው የአሜሪካ ብሄራዊ ጥቅም እና ፍላጎቶች ላይ በተቃራኒ መቆም መሆኑን በመግለጽ አስጠንቅቀዋል።
ይቁንም ከዚህ ቀደም በተደረጉ ድርድሮች ወደጎን ተገፍቶ የነበረው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት እና ባለሙያዎቹ ስለ አካባቢው ጉዳይ የካበተ ልምዳቸውን ተጠቅመው ድጋፍ እንዲያደርጉ እና አሜሪካ በሦስቱም ሀገራት ተቀባይነት የሚያስገኝላትን ገለልተኛ ስፍራን እንድትይዝ ሴናተሮቹ አሳስበዋል።