
ጎንደር: ጥር 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ከባለሃብቶች እና በውጭ ሀገራት ኑሮአቸውን ካደረጉ (ዲያስፖራ) አባላት ጋር በከተማዋ ባሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ዙርያ ያተኮረ የኢንቨስትመንት ፎረም አካሂዷል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ግርማይ ልጃለም የኢንቨስትመንት ልማት የበርካቶችን ተሳትፎ እንደሚጠይቅ በማንሳት ለዚህም ባለሃብቶች ያላቸው ሚና ጉልህ እንደኾነ አስረድተዋል።
ስምንት አልሚዎች በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብር እና እንዲኹም በአገልግሎት ዘርፍ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገቡ ከ29ሺህ በላይ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችሉ እና 33 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 142 ባለሃብቶች ፈቃድ ማውጣታቸውን አስታውቀዋል። ለ34 ባለሃብቶችም ብድር ማመቻቸት መቻሉንም ገልጸዋል።
ስምንት መካከለኛ ኢንደስትሪዎች ወደ ሥራ የገቡ መኾኑን ያነሱት መምሪያ ኀላፊው ሰባት ኢንዱስትሪዎች በተሳተፉበት ኤክስፖርት ከ53 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት መቻሉን አረጋግጠዋል።
ከ1ሺህ 400 በላይ የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉንም አስታውቀዋል። በተሰጣቸው የጊዜ ገደብም ወደ ሥራ መግባት ባልቻሉ 31 ፕሮጀክቶች ላይ እርምት መወሰዱን አረጋግጠዋል።
ለኢንቨስትመንት ውጤታማነት የመብራት፣ የውኃ፣ የስልክ እና የመንገድ መሠረተ ልማቶችን ለማሟላት መሠራቱንም አስረድተዋል።
ጎንደርን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ በጋራ እንደሚሠራም አረጋግጠዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ጎንደር በቱሪዝም እና በሌሎች ዘርፎች ለኢንቨስትመንት ምቹ የኾነ ሃብት ያላት ከተማ መኾኗን ጠቅሰዋል።
የጎንደር ሕዝብ ለልማት ልዩ ተነሳሽነት እንዳለው አረጋግጠው ይህን ዕድል መጠቀም ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የከተማዋን ገጽታ በማስዋብ፣ ለወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር እና በሌሎችም ከተማዋ ባላት ፀጋ መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል።
ጎንደርን አብረን እናልማ ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ከተማ አሥተዳደሩ ለኢንቨስትመንት ልማት ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ስለመኾኑም አንስተዋል።
በከተማዋ በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች በበኩላቸው ጎንደር ከተማ ያላት እምቅ የቱሪዝም ሃብት እና የግብርናው ሃብት በዘርፉ የሚሰማሩ ባለ ሃብቶች ውጤታማ እንዲኾኑ የሚያስችል መኾኑን ተናግረዋል።
ሃሳባቸውን ለአሚኮ ካጋሩ የውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል በሆቴል ቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩት አቶ መልካሙ በቀለ “ጎንደር ከተማ የቱስት መዳረሻዎችን የያዘች እና በጥምቀት በዓል በርካቶች የሚታደሙባት በመኾኑ በሆቴል ዘርፉ ውጤታማ ለመኾን ያስችላል” ብለዋል።
የአካባቢው ማኅበረሰብ ለልማት ያለው ተነሳሽነት እየሠሩ ላለው ሥራ ውጤታማነት ድርሻው የጎላ መኾኑንም አስታውቀዋል።
ከከተማ አሥተዳሩ ኢንድስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያገኙም አረጋግጠዋል።
ሌላኛው በከተማዋ ኢንቨስትመንት የተሰማሩት አቶ አባተ ሙሉ በከተማዋ ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
ጎንደር ጥንታዊ ከተማነቷ፣ ያላት የሕዝብ ቁጥር፣ የአየር ሁኔታዋ ምቹ መኾን እና ሌሎችም ምክንያቶች ከተማዋን ለኢንቨስትመንት ምቹ እንድትኾን እንዳደረጋት በመድረኩ ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ቃልኪዳን ኃይሌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
