የአንድ ተማሪ የፈተና ውጤት የተማሪው፣ የወላጅ እና የመምህራን የጋራ ጥረት ነው።

13
ባሕር ዳር: ጥር 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የመጀመሪያው ወሰነ ትምህርት የማጠቃለያ ፈተና ከሰሞኑ ይሰጣል።
ተማሪዎቹ የሚፈተኑበት ወቅት ሲቃረብ በከፍተኛ የጭንቀት ስሜት ውስጥ መግባታቸው የተለመደ ነው።
በባሕር ዳር ከተማ የደብረ ጺዎን ቅድስት ድንግል ማርያም አካዳሚ የ6ኛ ክፍል ተማሪ ፊሊሞን መርሃባ ለፈተና ቀደም ብሎ ራሱን እንዳዘጋጀ ነገረን።
በትርፍ ሰዓቱ ላይበራሪ በማንበብ እና ከጓደኞቹ ጋር በመኾን በመረዳዳት ራሱን እያዘጋጀም ነው።
የተማሪ ፊሊሞን መርሃባ እናት ወይዘሮ ሙሉነሽ ዓለምነውም ልጃቸው ጎበዝ ተማሪ መኾኑን ገልጸዋል። በተቻላቸው መጠን ለትምህርቱ የሚያስፈልጉትን ግብዓቶች በአግባቡ እንደሚያሟሉለት እና የትምህርት እና የጥናት ጊዜውን እንደማይሻሙትም ተናግረዋል።
ከቤት ውስጥ በአግባቡ የሚሰጠውን የቤት ሥራ እንዲሠራ እና በፕሮግራም እንዲያጠና ክትትል እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል።
የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ልቦና መምህር መሠረት አያሌው (ዶ.ር) የተማሪዎች የፈተና ውጤት ከፈተናው ላይ ካላቸው ግንዛቤ፣ ከዝግጅታቸው እና ከቤተሰብ ድጋፍ ጋር እንደሚያያዝ ገልጸዋል፡፡
አንዳንድ ተማሪዎች ከመጠን ያለፈ በራስ መተማመን ስለሚኖራቸው ፈተናን ቀለል በማድረግ ሊያዩት ይችላሉ፤ ሌሎች ደግሞ ተዘናግተው በመቆየታቸው ፈተና ሲቀርብ ጭንቀት ውስጥ ይገባሉ ነው ያሉት፡፡
ተማሪዎች በተፈጥሯቸው ከቤተሰቦቻቸው ድጋፍ በጣም የሚፈልጉ መኾናቸውን ዶክተር መሠረት ጠቅሰዋል። ወላጆች ከልጆቻቸው ከፍተኛ ውጤት መጠበቅ ብቻ ሳይኾን እገዛቸው እንደሚያስፈልጋቸው በመገንዘብ እገዛ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ተማሪዎች የሚማሩት ለራሳቸው ስብዕና፣ ለሕይወታቸው እና ለማኅበረሰቡ ሊያበረክቱት ከሚችሉት ድርሻ ጋር በማያያዝ እገዛ ሊደረግ እንደሚገባ ነው የጠቆሙት።
ተማሪዎች ውስጣቸውን በማጎልበት ፈተና ብቻ የሚያስጨንቃቸው አጀንዳ እንዳይኾን ማድረግ ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡
ፈተና ከባድ የሚመስለው ተማሪዎች የሚረዱበት እና የሚተረጉሙበት መንገድ መኾኑን ያስረዱት መምህሩ በዚህ ላይ የቤተሰብ ተሳትፎ ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
ወላጆች ልጆቻቸውን በመቆጣጠር አለያም በሙሉ ጥገኛ እንዲኾኑ በማድረግ ሳይኾን ጤናማ እና ቀለል ያሉ ምግቦችን እንዲመገቡ ማድረግ እና ስሜታቸውን በመከታተል የሞራል ድጋፍ መስጠት ይገባል ነው ያሉት።
ተማሪዎች በመጀመሪያ ደረጃ በእገዛ ሊደገፉ ቢችሉም ቀስ በቀስ እገዛው እየቀነሰ የራሳቸው መተማመን እንዲገነባ ማድረግ አስፈላጊ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡
በሁሉም ነገር በእገዛ ጥገኛ የተደረጉ ተማሪዎች በተለይም በሀገራዊ ፈተናዎች ላይ ብቻቸውን ሲኾኑ የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚከብዳቸው ጠቅሰዋል፡፡
መማር ግዴታ ቢኾንም፣ የስኬት አንድ መንገድ ብቻ አይደለም ያሉት ዶክተር መሠረት የልጆች ተፈጥሯዊ ችሎታ፣ ፍላጎት እና መክሊት ተገናዝቦ መመራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡
የተማሪዎች ሥነ ልቦናዊ ዝግጅት ራስን ማሸነፍ ቀዳሚው ድል ነው ያሉት ዶክተር መሠረት ፈተና ማለት ዕውቀትን የመመዘኛ ስልት እንጅ የግለሰብን ማንነት እና ዋጋ መወሰኛ አይደለም ብለዋል።
ተማሪዎች አልችልም የሚለውን ስሜት አጥፍተው እችላለሁ በሚለው መተካት እንዲችሉ መታገዝ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ቀደም ብለው የተሠሩ የፈተና ጥያቄዎችን ደጋግሞ በመሥራት በራስ መተማመንን ማዳበርም አስፈላጊ እንደኾነ አብራርተዋል።
ተማሪዎች ለማጥናት ብለው እንቅልፋቸውን መቀነሳቸው ለጭንቀት እና ለመርሳት ችግር ሊዳርጋቸው ስለሚችል በሚገባው ልክ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በቂ እንቅልፍ መተኛት እና አዕምሮን ዘና ሊያደርጉ የሚችሉ ጨዋታዎችን እና አካላዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ትኩረታቸው እንዲጨምር ያደርጋል ነው ያሉት።
ፈተና ከመጀመሩ በፊት እርጋታ በተሞላበት አኳኋን በጥልቀት መተንፈስን መለማመድ፣ ጥያቄዎችን በደንብ ማንበብ እና ቀለል ያሉትን አስቀድሞ በመሥራት ሞራልን መገንባት ያስፈልጋልም ነው ያሉ።
በፈተና ወቅት ወላጆች ከሌሎች ቀናቶች በተለየ ልጆቻቸውን ትኩረት ሰጥተው ሊከታተሏቸው ይገባል ብለዋል።
ከፍተኛ ውጤት ካላመጣችሁ ብሎ ማስጨነቅም ለከፍተኛ ድንጋጤ እንደሚዳርጋቸው አስገንዝበዋል።
ወላጆች የቻሉትን እንዲያደርጉ በማበረታታት ከጎናቸው እንዳሉ በመንገር ማጀገን እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የፈተና ውጤት የአንድ ተማሪ የትጋት ውጤት ቢኾንም፣ ውጤቱ ግን የተማሪው፣ የወላጅ እና የመምህራን የጋራ ጥረት ነፀብራቅ እንደኾነም አስረድተዋል።
ተማሪዎች ከጭንቀት ነፃ ኾነው ወደ ፈተና ሲገቡ በአዕምሯቸው የቋጠሩትን መረጃ በቀላሉ ማውጣት እና ውጤታማ ይሆናሉ ብለዋል።
ዘጋቢ፡- ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleየጥምቀት እና የከተራ በዓል ስኬታማ ነበር።
Next articleበባሕር ዳር ከተማ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመጪው ምርጫ ዙሪያ እየመከሩ ነው።